




በኢትዮጵያ አየር መንገድ በየአመቱ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራው በረራ ዛሬ ማታ ወደ እንግሊዝ ሀገር ለንደን ጋትዊክ ያቀናል::
ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ማርች 8 አስመልክቶ በአየር መንገዱ በሴቶች ብቻ የሚመራ ጉዞ ወደተለያዩ መዳረሻዎች የሚበር ሲሆን ዘንድሮም ለ9ኛ ጊዜ “ሴቶችን በማብቃት አፍሪካን ማስተሳሰር” በሚል መሪ ቃል ወደ ለንደን ለሚጓዙ የሴት ልዑካን ቡድን ሽኝት ተደርጓል::
በሽኝት መረሃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳሬን ዋሊች በየደረጃው ያሉ የአየር መንገዱ ሴት አመራሮች፤ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል::
በዋና አብራሪ ቃልኪዳን ግርማ በሚመራው በዚህ ጉዞ ረዳት አብራሪ፤ ቴክኒሻን የበረራ አስተናጋጆች የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሁሉም ሴቶች መሆናቸው ታውቋል::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት አየር መንገዱ የሴቶችን ተሳትፎ በማበረታታት አካታች በሆነ መንገድ በርካታ ሴት አመራሮችና ባለሙያዎችን ይዞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል::
በዚህም አየር መንገዱ የሴቶችን ተሳትፎ በማስቀጠል ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ ይተጋል ብለዋል።
በአየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራው ይህ በረራ ከዚህ ቀደም ወደ ባንኮክ፣ ኪጋሊ፣ ሌጎስ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ኖርዌይ፣ ቦነስ አይረስና ዛንዚባር መጓዙ ይታወሳል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
