ሰልጣኝ አብራሪዎች የኢትዮጵያን አየር ኃይል የስኬት ጉዞ የሚያስቀጥሉ ተረካቢ ትውልድ ናቸው – ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ::

Spread the love

ሰልጣኝ አብራሪዎች የኢትዮጵያን አየር ኃይል የድልና የስኬት ጉዞን የሚያስቀጥሉ ተረካቢ ትውልድ መሆናቸውን በመገንዘብ ሙያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ እና በቴክኖሎጂ ራሳቸውን ለማብቃት ይበልጥ መዘጋጀት አለባቸው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

ዋና አዛዡ በ L-39 እና በሴሲና 172 ስኳድሮኖች የሶሎ በረራን ስልጠና በሚገባ አጠናቀው ወደ ቀጣዩ ምዕረፍ የተሸጋገሩ ሰልጣኝ አብራሪዎችን በአየር ኃይል በረራ ትምህርት ቤት ተገኝተው አበረታተዋል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለአብራሪ ሰልጣኞቹ በአስተላለፉት መልዕክት ለአንድ በበረራ ሙያ ሀገሩን ለማገልገል ሀሳብ ላለው የበረራ ተማሪ ሶሎን መብረር የመጀመሪያው ምዕራፍ ማብሰሪያ እንጂ በአቭዬሽን ሳይንስ የመጨረሻው ግብ አለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በዚህ የሙያ ዘርፍ ወደፊት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀው፤ የአየር ኃይል የድልና የስኬት ጉዞ ራዕዩ ከግብ እንዲደርስ እንዲሁም የትውልድ ቅብብሎሹንም ለማስቀጠል ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

ጥብቅ ወታደራዊ ዲስፕሊን እና ሙያዊ ስነ ምግባርን እንደ መርህ መከተል በሁሉም አብራሪዎች ዘንድ የቅድሚያ ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ፤ ወጣት አብራሪዎቹ ተልዕኳቸውንም ከጥልቅ ሀገራዊ ፍቅር በሚመነጭ ታማኝነት እና የሀላፊነት መንፈስ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአየር ኃይል በረራ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ጃምቦ አዛገ በበኩላቸው፤ በተቋማዊ ሪፎርሙ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች መካከል የበረራ ስልጠና በዋነኝነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የበረራ ትምህርት ቤቱም ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አሁን የሶሎ በረራን ስልጠና ያጠናቀቁትን ጨምሮ ቀድሞ ከነበረው በተሻለ የአቅም ደረጃ አብራሪዎችን በማፍራት የአየር ኃይልን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ይገኛል ማለታቸውን ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሶሎ በረራ በአብራሪነት ህይወት ልዩ ትርጉም ያለው ወሳኝ ተግባር መሆኑን እና ወደፊት ሀገራቸውንም በአብራሪነት የሙያ መስክ ፍፁም በሆነ ታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየት የሰጡ ሰልጣኝ አብራሪዎቹ ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *