
በአፍሪካ ሽብርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ግጭት፣ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥና ሌሎችም የጸጥታ ሥጋቶች የአህጉሪቷ ፈተና ሆነው በመቀጠላቸው ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅላቸው እንደሚገባ የአፍሪካ ኅብረት ገለጸ።
የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሠላምና ደኅንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴኦዬ፤ ከ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የአህጉሪቱን የጸጥታ ጉዳዮች አስመልክተው ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፣ በአፍሪካ ሽብርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ የአመጽ ድርጊቶች አሁንም በአፍሪካ ፈተና ሆነው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህ ችግሮች የመከሰት ምጣኔያቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው አሁን ላይ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት በአህጉሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው ያብራሩት።
አፍሪካ ኅብረት ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥ እንደማይታገስ ገልጸው ስድስት አገራትም ይህንን ተግባር በመፈጸማቸውና የኅብረቱን የዲሞክራሲ መርሆዎች በመጣሳቸው ከአፍሪካ ኅብረት ተሳትፏቸው መታገዳቸውን ገልጸዋል።
ያም ሆኖ ኅብረቱ በእነዚህ አገራት የፖለቲካ ሽግግር ማድረግ በአገራቱ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ዳግም ለመመለስ፣ የሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ መብት እንዲሁም መሰረታዊ የነጻነት መብቶች እንዲከበሩ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
በህጉሪቷ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ህገ መንግስታዊ አሰራርን አክብሮ መንቀሳቀስ የግድ ይላል ያሉት ኮሚሽነሩ ከህገ መንግስታዊ አሰራር ውጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ በምንም አይነት መልኩ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጽኖት ሰጥተዋል።
በአፍሪካ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው ከህግ ውጭ የሆኑ ተግባራትን ግን በፍፁም አንታገስም ሲሉ አረጋግጠዋል።
የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም በሰጡት ማብራሪያ፤ ግጭት አላስፈላጊና ግጭቱ በሰላም እንዲቋጭ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ጠመንጃቸውን አስቀምጠው ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ኅብረትም በሱዳን ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለው ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለውን አለመግባባት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ጉዳዩን በውይይት መፈታት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በአፍሪካ ሰላምን ለማስፈንና የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ለማስቻል የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ያረጋገጠ የሰላም ግንባታ ሥራዎች ኅብረቱ አበክሮ የሚሰራባቸው መስኮች መሆኑንም ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።
ከዚህ አንጻር በአፍሪካ መሪዎችን ጭምር ዘርፉን እንዲመሩት በማድረግ ሰላም ለማረገጋጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመው በሠላም ላይ የሚሰሩ አካላት፣ ተቋማትና አሰራሮች በአህጉሪቱ ሠላም እንዲጸና ተሳትፏቸው መጠናከሩን ጠቅሰዋል።
በአህጉሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የተቀሰቀሱትን የጸጥታ መደፍረሶች እልባት ለመስጠት በጋራ እንዲሚሰሩ መሪዎች በሰብሰባቸው ትኩረት አድርገው መወያየታቸውን ጠቁመው በአፍሪካ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማምጣት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
