
37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
ጉባኤውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፥ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የእንግዶች ቆይታ ያማረ እንዲሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
በሶማሊያ መንግስት በኩል የቀረበው ውንጀላ ኢትዮጵያ ለእንግዶች ያደረገችውን እንክብካቤ የማይመጥን ነው ብለዋል።
ሁሉም መሪዎች ያለ ልዩነት አቀባበልና መስተንግዶ እንደተደረገላቸውም ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ እንደ አስተናጋጅ ሀገር ሙሉ ኃላፊነት ወስዳ መስራቷን ገልጸዋል።
የጦር መሳሪያ ይዞ ወደ ጉባኤው ለመግባት መሞከር፣ ትኩረት ለመሳብና ያልተገባ ወቀሳ ለመሰንዘር ባለመ መልኩ ክስ መቅረቡ አስገራሚ እንደነበረ አብራርተዋል።
ችግሩ በህብረቱ የጸጥታ አካላት ብስለት መፈታቱን ተናግረዋል።
ጉባኤውን ለማስተናገድ ከተደረገው ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የተሳካ ስራ መሰራቱን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በጉባኤው ዋና ዋና ስኬቶችን ማንጸባረቅ ተችሏል ብለዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።
