በአፍሪካ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊና አካታች የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት አህጉራዊ ልማትና እድገት ማፋጠን ይገባል::

Spread the love

በአፍሪካ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊና አካታች የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት አህጉራዊ ልማትና እድገትን ማፋጠን እንደሚገባ በትምህርትና ልማት ዘርፍ የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት ገለጹ።

37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።

የሕብረቱ ጉባዔ መሪ ሃሳቡን ትምህርት ላይ ማድረጉ በተለይ በቴክኖሎጂና በተማረ የሰው ኃይል እጥረት ወደ ኋላ የቀረውን አህጉር እድገት ለማፋጠን መሆኑ ተገልጿል።

በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው በልማትና ትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ ተቋማት ኃላፊዎች፤ በአፍሪካ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊና አካታች የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት አህጉራዊ ልማትና እድገትን ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት ችግሮች፣ የመሠረተ-ልማት እጥረት፣ የመንግሥታት ትኩረት ማነስና ሌሎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ተዳምረው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸውን ገልፀዋል።

በአፍሪካ አሁን ላይ ከ98 ሚሊየን በላይ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆናቸው በአህጉሪቷ ትልቅ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት መሪዎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል።

በዚሁ ዙሪያ ላይ የሚሰራውና ለትርፍ ያልተቋቋመው የግል ድርጅት የአፍሪካ ብልጽግና ኔትዎርክ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሙሴ ኦፎሪ-አታ አፍሪካ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አዲስ የትምህርት ሥርዓት ያስፈልጋታል ብለዋል።

የአፍሪካ የወደፊት የትምህርት ሥርዓት በተለይም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና በሒሳብ ሙያዎች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት አስተዳዳሪና የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ፤ የአፍሪካን ልማት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት ሥርዓት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ለዚህም ሲባል የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በትምህርት ላይ ማተኮሩን አድንቀው፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት የአህጉሪቷን ዜጎች ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የፕላን ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ሕብረት ዳይሬክተር ዴር ሳፑሙ፤ የአፍሪካ ሕብረት ትምህርት ላይ የያዛቸው ዕቅዶች እንዲሳኩ ተቋማቸው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይም ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል።

በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ዙሪያ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ጥረቶችን አንስተው፤ በተለይም ሴቶችን በማስተማርና ወደ ኃላፊነት በማምጣት የሚታዩ ውጤቶች መገኘታቸውን አድንቀዋል።

የአፍሪካ አገራት ከዓመታዊ በጀታቸው ቢያንስ 20 በመቶውን ትምህርት ላይ ቢያውሉ በዘርፉ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ጠቁመው፤ ከምንም በላይ ለትምህርት ትኩረት እንዲሰጡም አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *