

በሀገራችን ኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነት በመጨመር የግብርና ክፍሌ ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሰፊ ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነትና ምርታማነት በምርምር የተረጋገጡና የተደገፉ ለማድረግ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ዋነኛውና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ክልላችን ሲደራጅ ያለውን አቅም ለይቶ በማወቅ በሁሉም ዘርፎች የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ለማሟላት የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ ግብ ጥሎ ወደ ስራ ተገብቷል። ከዚህም መነሻ በክልሉ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም በግብርና ዘርፍ የተጀመሩ ጅምር ስራዎች አበረታች፣ይበል የሚያሰኙና መጠናከር የሚገቡ ናቸው።
በክልሉ የሚገኙ አብዘኛ አፈሮች አሲዳማ ከመሆናቸው ጋር የተነሳ በግብርና ምርት መጨመር ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ክልሉ ከተደራጀ በኋላ ችግሩን ለይቶ ለችግሮች እልባት ለመስጠት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮግራሞች ተቀርጾ አፈርን በኖራ ማከም፣የተፈጥሮ ካልሸም ይዘት ያላቸው የአፈር ማዳበሪያዎችን፣ ቨርሚ ኮምፖስት በማዘጋጀት አርሶ አደሮችን በማሳተፍ አፈሩ ለምነት እንዲጠብቅና እንዲሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ በCALM እና OCP ፕሮጀክት የተሰሩ ስራዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም ተብሏል።
በክልሉ በዋናነትም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በምርምር የተደገፉ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ፣ ማፍለቅ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን አባዝቶ ለምርጥ ዘር ድርጅትና ለተደራጁ አባዝ አካላት ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም ገበያን የሚመራ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ለማስፋፋትና የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅ የሚል ራዕይ ይዞ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን የመፈጸም ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንዳለም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ አስታውቋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ በኋላ በተለይም ቀደም ሲል በነባሩ ክልል በነበረው ወቅት በአንድ ማዕከል ብቻ ሲከናወን የነበረውን ተግባራትን ጭምር ይዘው ወደ ስራ እንደገባም አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት ለግብርና ዘርፍ ከሰጠው ትኩረት አንፃር የታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም በጀት በመመደብ የማዕከሉ ግንባታ እንዲጀመር ተደርጎ የግንባታ አፈጻጸሙ አሁን ላይ 80% እንደደረሰና በቀሪ ግማሽ ዓመት ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደምጀምር እየተሰራ ያለው ስራ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት እንደ ትልቅ ትሩፋት ተብሎ ይወሰዳል።
ተቋሙ በስድስት ምርምር ክፍሎች እንዲደራጅ ተደርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በስድስቱም ክፍሎች ቀደም ሲል በነበረው ማዕከል ማለትም በቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል 32 የምርምር ስራዎችን በማጠናቀቅ አብዛኞቹ ፓኬጅ ተዘጋጅተው ለተጠቃሚዎች በአግባቡ እንደደረሱና ሌሎች በዝግጅት ላይ እንዳሉም አንስተዋል።
ባለፉት ጊዜያትም በበጀት እጥረት ምክንያት ሳይሰሩ የቆዩትን እንደአስፈላጊነታቸው 129 የምርምር ስራዎችን በቀጣይ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ በሰፊው እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም በቦንጋ ምርምር ማዕከል ካፋ፣ቤንች ሸኮ፣ሸካና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በትኩረት እየተመራ ይገኛል ።
የታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል ግንባታ ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ ስራውን እስኪጀመር ድረስ በዳውሮና በኮንታ ዞኖች ጊዜያዊ ባለሙያ በመመደብ ባለፈው ክረምት የተጀመሩ ጅምር ስራዎች አበረታች ናቸው።የተጀመሩ ተግባራትም በረጅም፣መካከለኛና በአጭር ጊዜያት የሚፈጸሙ መሆናቸውም ተገልጿል።
ክልሉ በርካታ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ቢሆንም አከባቢው በምርምር ዘርፍ ምንም ሳይታወቅ ትኩረት ሳይሰጠው በአንድ ማዕከል ብቻ ሲሰራ ቆይቷል።
ክልሉ በስድስቱም ዞኖች ስፊ የመልማትና ምርታማነት አቅም ፣ምቹ ስነምህዳር እንዲሁም አብዛኛው ሰብሎች መብቀልና ምርት የመስጠታቸው ዕድሉ ስፊ እንደሆነም ያብራሩት አቶ አማኑኤል ዓለሙ ኢንስቲትዩቱ በሰብል ዘርፍ በቦቆሎ በማሽላ፣በስንዴ፣ገብስ፣ሩዝ፣በምግብ ድንች፣ቦሎቄ እና በበቄላ ሰብል ላይ የተጠናቀቁ የምርምር ስራዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆናቸውም ተብራርቷል።
በሙዝ፣አቡካዶ፣በሽንኩርትና በቲማቲም የምርምር ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና ክልሉ የቡና መገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጠቀሜታ ያላቸውን ዘረመሎችን መለየትና የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚታየውን የምርጥ ዘር እጥረት ለመፍታት በዘንድሮ ክረምት በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ 78 ሄ/ር መሬት ላይ ስንዴ፣አተር፣ባቄላ ፣ሩዝ ዘሮችን አባዝቶ የአርሶ አደሩን የዘር ፍላጎት ለማሟላት በሚችል መልኩ የቅድመ መስራች ዘር መቋቋም ስራ መስራት ተችሏል ብለዋል።
ለአብነትም በኮንታ ዞን አርሶ አደሩ ዘር የማባዛት ዘዴ አውቀው እውቀትና አሰራሮችን ተከትለው ከተቋማት ጋር በመደራጀት በኩታገጠም ዘሮችን በማባዛት የዘር እጥረት መፍታት እንዲችሉ 35 አርሶ አደሮችን ያሳተፈ በ50.5 ሄ/ር መሬት ስራው መከናወኑንም አቶ አማኑኤል ዓለሙ ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ ረገድ ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጡ እስከ ስድስት ወር ብቻ ለ1063 አርሶ አደሮች ፣ከፍተኛ አመራሮችና ተቋማት ቴክኖሎጂ እንዲተዋወቁ የማድረግ ስራ በተቋሙ እንደተሰራም ገልጸዋል።
በተጨማሪም አከባቢው የእንስሳት ቀጠና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ትኩረት ሰጥተው እየሰራ ይገኛል በዚህም በግ፣ፍየል፣በንብና በዶሮ ምርታማነት 24 የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው።25 የምርምር ስራዎች ቀደም ሲል ተጠናቀው ፓኬጅ ተደርጓል ብለዋል ።
የቦንጋ በግ ዝሪያ ከክልል፣ከሀገር አልፎ በአለም ደረጃ ዝሪያው እንዲታወቅ ከዘር ልየታ ጀምሮ ስራዎች በሰፊው እንደተሰሩና የተለያዩ የምርምር ስራዎች በዝሪያ ማሻሻያና በሰው ሰራሽ በማዳቀል ዘር የማዘጋጀት ስራ የተሳካ ሙከራዎች እንዳሉም ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህም ከቦንጋ በግ ዝሪያ የተሻሻሉ ከ3600 በላይ አውራ በጎችን በመምረጥ በክልሉ ውስጥና ውጭ የማሰራጨት ስራ ተሠርቷል ብለዋል።
በዚህም ለዘር የማይሆኑ አውራ በጎችና እናቶችን በመለየት ለ3 መቶ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠር እንደተቻለና ክልሉ ካለው ከተፈጥሮ ሀብት አንፃር የማር ምርቱና ጥራቱ በዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆንና ምርቱ እንዲተዋወቅ በምርምር የተደገፈ ውጤቶች እየወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በዶሮ ምርታማነት ሀገረሰብ ዶሮዎች ከማሻሻል ምርታማነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ክልሉ ከተደራጀ በኋላ እንደትልቅ ዕድል የሚወሰደው ክልሉ የራሱን ሀብት በራሱ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለችግሮቹ መፍትሔ ማበጀት የክልሉ መደራጀት ለዘርፉ ትልቅ አቅም ነው።
የክልሉ መንግስት ከበጀት ጀምሮ በቅርበት ዕቅዶችን በጋራ ማቀድ፣ተከታትለው ማስፈፀምና ያለበትን ደረጃ በወቅቱ መገምገም በስራዎች ምክረሀሳብ መስጠትና በቴክኖሎጂ እያስደገፈ ያለው ስራ ሊጠናከር የሚገባና ኢንስቲትዩቱ የጀመረውን የምርምር ስራዎችን አጠናክረው በማስቀጠል ከክልል አልፎ በሀገር ደረጃ የምግብ ፍላጎት መመለስ እንዲያስችልም ያግዛል ብለዋል አቶ አማኑኤል።
በሀገር ደረጃ በምርምር ምርታማነታቸውና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አከባቢ ማምጣት በአካባቢ ያሉትን በመለየት በተለያዩ በግብርና ምርምር ተቋማትና ማዕከላት ድጋፍ ከሚሰጡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር ሰፊ ስራዎችን ለማከናወን ዕቅድ መያዙም ተብራርቷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በክልላችን መከናወን የሚገባቸው ተግባራትን በቴክኖሎጂ ፣በእውቀትና በተለያዩ ነገሮች ኢንስቲትዩቱን እየደገፈ ያለውን ያልተቋረጠ ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይም መጠናከር ይገባል ብለዋል።
ተቋሙ ወቅቱን ጠብቆ የሚመራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስራዎች ማነቆ እንዳይፈጠር በጀትና ፋይናንስ ጋር ያሉ ክፍተቶች እንዲፈቱ ያነሱት አቶ አማኑኤል ዓለሙ ለስራው ስኬታማነት ባለድርሻ ተቋማትና አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፏል።
በፍቅር ከበደ
