በኢትዮጵያ የሚተገበረው የሽግግር ፍትሕ በደሎችን በማከም ሠላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገርን ለመገንባት ያለመ ነው – ፍትሕ ሚኒስቴር::

Spread the love

በኢትዮጵያ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሚፈጸመው የፍትሕ ስርዓት በደሎችን በማከም ሠላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገርን ለመገንባት ያለመ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ አለመግባባትና ግጭት መፈጠራቸውን ተከትሎ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ እንዳስፈለገም ገልጿል።

በዚህ መነሻነትም በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ችግሮችን በእርቅ፣ በካሳ፣ በይቅርታና ተጠያቂነት መርህ ምላሽ ለመስጠት የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ዝግጅት ስራውን አጠናቋል።

የፍትሕ ሚኒስቴርም በረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሀን፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ያለፈባቸው የግብዓትና ምክረ ሃሳብ የማሰባሰብ ሂደቶች ቀጣይ ለሚወጡ ፖሊሲዎች ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ምክክር ማድረግ ያስፈለገውም፥ ሰነዱን በማጥራትና በማዳበር ግልጽ የሆነ ፖሊሲ ለማጽደቅ መሆኑን አንስተዋል።

በፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ እና የቀድሞ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት የባለሙያዎች ቡድን አባል ሲሳይ አስፋው፤ በሰነዱ ሰብዓዊ መብት የጣሱ አካላት የሚጠየቁበት፣ እውነት የሚወጣበትና ተጎጂዎች የሚካሱበት ሥርዓት እንደሚካተት ተናግረዋል።

በዚህ የፍትሕ ስርዓት በደልና ቁርሾዎችን በመፍታት የተሻለ ነገን የሚፈጥር ማህበረሰብ መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ያካተተው የፍትሕ ስርዓት የተፈጸሙ በደሎችን በማከም ሠላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገርን መገንባት ዓላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ሴት አባላት ጥምረት ሰብሳቢና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል ነቢሃ መሀመድ፤ የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ጸድቆ እንዲተገበር ፓርቲያቸው የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረ-እግዚአብሔር በበኩላቸው፤ በብሔራዊ ምክክርና በሽግግር ፍትሕ በደሎችን ማከም እንደሚቻል ደቡብ አፍሪካን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችን በስኬት የቋጨችው ሰላማዊ ምህዳር በመፈጠሩ መሆኑን ገልጸው፥ በኢትዮጵያም የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የተበደሉ ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊነት ወሳኝ ነው ያሉት የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አላምረው ይርዳው ናቸው።

ረቂቅ ሰነዱም ተግባራዊ ሲሆን ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደገም ትምህርት የሚሰጥና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሲተገበር የተሟላ የዴሞክራሲ ሥርዓት ያለባት፣ የተበደሉ ዜጎች የሚካሱባት፣ ሰላም፣ መረጋጋት፣ እርቅ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አይነተኛ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *