በክልሉ በቀጣይ ለሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ::

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሆልቲካልቸር ሰብሎች ላይ በቀጣይ ለሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።

በይፋዊ ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ ፕሮጀክቱ በክልሉ የግብርና ስራዎችን ውጤታማ የሚያደርግ ነው ብለው ለዚሁ ተግባር ማሳኪያ 97 ሚሊዮን 469 ሺህ 824 ብር በጀት የተያዘለት መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጀቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ወ/ሮ ወሰነች ተናግረዋል።

የSNV Holti Life ፕሮጀክት የደቡብ አከባቢ ሪጅናል ማናጀር ወ/ሮ ዓለምጸሀይ ገነት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለሶስት አመታት በሁለት ዞኖች በዘጠኝ ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን አቅም በማጎልበት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከካፋ እና ከቤንች ሸኮ ዞኖች በተመረጡ ዘጠኝ ወረዳዎች ላይ እንደሚጀመር ያሳወቁት አቶ አሸናፊ በቀጣይ ከዳውሮ ዞን ሁለት ወረዳዎችን በመጨመር በክልሉ በ11 ወረዳዎች ላይ ተጠናክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አማካሪና የግብርና ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ ፕሮጀክቱ ከኔዘርላንድ ልማት ድርጅት በተገኘ የበጀት ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰው ክልሉ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ የመልማት አቅም ያለው በመሆኑ ከሞዴል አርሶአደሮች ሌሎች ትምህርት በመውሰድ አቅማቸውን ገንብተው ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያግዝ ፕሮጀክት መሆኑን አብራርተዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *