




በግምገማው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ መቀንጨርን ለመከላከል በምግብና ስርዓተ ምግብ በብዝሃ ሴክተሮች በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በክልሉ ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም በስምንት ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ አልማው በፕሮግራሙ አባል የክልል ቢሮዎች የተሳተፉበት ሲሆን በዚህም በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል ።
በምግብ ስርዓትና ስርዓተ ምግብ ፕሮግራም በችግር ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን በመለየት ያልተመጣጠነ የምግብ አጠቃቀም ስርዓትን በመቅረፍ አምራችና ጤናማ ትውልድ እንዲኖር ማድረግ ይገባል ያሉት ኃላፊው በፕሮግራሙ ሂደት በርካታ ስራዎች ቢሰሩም መረጃን ከማደራጀት፣ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ከማጠናከርና ሀብት ከመመደብ አንጻር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ሊቀረፉ እንደሚገቡ አሳስበዋል።
የክልሉ የምግብ ስርዓትና ስርዓተ ምግብ አስተባባሪ አቶ ማቴዎስ ማልዳዬ ፕሮግራሙ በዋናነት ካልተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የምግብ እጥረትና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
የምግብ እጥረት ችግር ሰለባ የሆኑትን ህጻናት፣ አጥቢና ነፍሰ ጡር እናቶች እንዲሁም የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየትና በመደገፍ ጤናቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የተነደፈ ፕሮግራም እንደሆነ ያብራሩት አቶ ማቴዎስ ብዝሃ ሴክተሮች በፕሮግራሙ አተገባበር ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት በተጠያቂነት ስሜት ተግባሩን ሊመሩ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የፕሮግራሙ የ2016 ግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን የብዝሃ ሴክተር አባላትም የዘርፉን ስራ ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል ባለፈው የስድስት ወራት አፈፃፀም ላይ የታዩ ክፍተቶችን በማረም የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥሉ በአስተያየታቸው ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ስራውን ውጤታማ ለማድረግ እንዲያስችል ተቋማቱ የሚመሩበት የመግባቢያ ሰነድ ቀርቦ በመተቸት በጋራ ተፈራርመዋል።
በታጠቅ አበበ
