


በሸካ ዞን በሁሉም ከተማና ወረዳ አስተዳደሮች ሲደረገ የነበረው የብልጽግና ፓርቲ አባላት ዞናዊ የማጠቃለያ ኮንፈረንስ ተጠናቋል።
“ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ፓርቲው በግማሽ የምርጫ ዘመን ያከናወናቸውን ተግባራት በማጠናከር ጉድለቶችን በማረም በቀጣይ ጊዜያት አባላቱና አመራሩ ሚናቸውን በተገቢው እንዲወጡ ተጠይቋል።
የሸካ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ በመድረኩ እንደገለጹት ፓርቲው በምርጫ ወቅት ለህዝብ የገባቸውን ቃሎችን የተከናወኑትና ያልተከናወኑት በመለየት በቀጣይ ምላሽ ለመስጠት መትጋትና በተለይም በዞኑ በሰላምና ጸጥታና በሌሎችም ዘርፎች ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ስከቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ላይ አባላት ርብርብ ሊያደርጉ እንዲገባም ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ ቆመው የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የማስጀመር፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የስንዴ አብዮት ስኬት እንዲሁም በአከባቢያችንም ደረጃ የተጀመሩት የሰላም፣ ልማትና የብልጽግና ጉዞ አብዮቶችን በዋናነት አንስተዋል።
በዞኑ ከለውጡ ወዲህ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በጥበብና በብስለት በማለፍ በሁሉም ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች አበረታች መሆናቸውን የገለጹት አቶ አለማየሁ እነዚህም በቀጣይ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል አባላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ የአብዮት መንገድን ሳይሆን የለውጥ መንገድን የተከተለ ፓርቲ መሆኑን ጠቁመው በለውጡ ወቅት ያጋጠሙ በርካታ ፈተናዎችን በመሻገር ሀገርን ከብተና በመታደግ ያስቀጠለ በመሆኑ ይህንንም በመረዳት ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።
በኮንፈረንሱም ለክልል ማጠቃለያ ኮንፈረንስ የሚሳተፉት አባላት የተመረጡበትና ባጠቃላይ እንደ ዞን ሁለት ሺህ አምስት መቶ በላይ አባላት፣ ከአንድ ሺህ ሃምሳ በላይ ህዋሳትና እንዲሁም አንድ መቶ ሃያ ስምንት መሰረታዊ ድርጅቶች በተዋረድ በሁሉም መዋቅር እንዳሉ ከዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
