የሸካቾ ብሄረሰብ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር መሪ በዓለ ስመት ተካሄደ።

Spread the love

የሸካቾ ብሄረሰብ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር ንግሥና ስነስርዓት በሸካ ዞን የነገሥታት መናገሻ በሆነችሁ ጥንታዊቱ የአንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ ተካሂዷል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካሉት ስድስት የአስተዳደር መዋቅሮች አንዱ የሆነው የሸካ ዞን የድንቅ ተፈጥሮ፤ የብዙ ታሪክና ባህላዊ ዕሴት ባለቤት የኾነ ዞን ነው።

“ባህላችን ለአብሮነታችንና ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል በተካሄደዉ የሸካቾ ብሄረሰብ የባህል ሲምፖዚየም የተለያዩ ኩነኔቶች ተከናውነዋል።

ሲምፖዚየሙ በቀዳሚነት ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የብሄረሰቡን የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር መልሶ በማደራጀት አደረጃጀቱን የሚመራ መሪ (ንጉሥ) ሹሟል።

የባህላዊ አስተዳዳሪ መዋቅሩ ” ታቶ” (ንጉሥ)፤ “ካታራሻ”ወይም ገዥ እና ሰባት “ምክረቾ” (የህዝብ እንድራሴ) የሚመራ ሆኖ እስከታችኛው መዋቅር በየደረጃው ተደራሽ የሆነ መሆኑ ተጠቁመዋል።

በበዓለ ስመቱ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ እንደገለጹት የሸካቾ ብሔረሰብ የአስተዳደር መዋቅር ለዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ስረዓት የጎላ ሚና ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

ብሄረሰቡ ለረጅም መቶ ዓመታት በዚህ የባህላዊ የአስተዳደር ስረዓት ይመራ እንደነበረ ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው በግዛት ማስፋት ጦርነት ተቋርጦ የቆየ የባህላዊ አስተዳደር ስርዓቱ አሁን በተፈጠረው ብዝሀዊ አካታች ስረዓት ዳግም የተመለሰ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሲምፖዚየሙ ዓላማ በልማትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅሩ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው

የባህላዊ አስተዳደር መዋቅሩ ህዝብ ለህዝብ በማቀራረብ ሠላም ለማስፈን፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የባህላዊ እውቀትና ዕሴቶች ህዝቦችን በማቀራረብና ችግሮች በመፍታት የጎላ ሚና እንዳላቸው ይታመናል ያሉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በዚህም መሠረት በክልሉ ሁሉም አከባቢ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች የየራሳቸው ታሪክና ባህል ጠብቀው ማቆየታቸው አሁን ላይ መንግሥት ለሚያከናው የሠላም ግንባታ፣ የልማትና ፀጥታ አስተዳደር፣ የመልካም አስተዳደር ተግባራት የአምበሳውን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት እውቅና ይሰጣል ብለዋል ።

የክልሉ መንግሥት የሸካቾ የባህላዊ አስተዳደር ስረዓት ጨምሮ በክልሉ በሌሎች ህዝቦች ዘንድም ያሉ ባህላዊ ዕሴቶችንና ታሪኮች ለማጠናከርና ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ገልጸዋል።

በሸካቾ ብሄረሰብ የባህል ሲምፖዚየም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች፣ የአከባቢው ምሁራን፣ ተጋባዦች እንግዶች የብሄሩ ተወላጆች ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *