
አዲስ አበባ፦ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሰባት ወራት ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ። አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን ገቢና ወጪ ጭነት እንዲሁም ከ115 ሺህ በላይ መንገደኞች ማጓጓዙን ማኅበሩ ጨምሮ ገልጿል፡፡
በማኅበሩ ከፍተኛ የእቅድና የፕሮግራም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ፍስሐ መብራህቶም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት ሁለት ቢሊዮን 256 ሚሊዮን 459 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት ሁለት ቢሊዮን 158 ሚሊዮን 333 ሺህ ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ያነሱት አቶ ፍስሐ፤ የእቅዱን 104 በመቶ በማሳካት ከሚጠበቀው በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
አቶ ፍስሐ አክለውም፤ ባለፉት ሰባት ወራት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ጭነት ለማጓጓዝ ታቅዶ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን ጭነት ተጓጉዟል ያሉ ሲሆን፤ የሚፈለገው ያህል ጭነት ያልተጓጓዘው በነበረው የፀጥታና የደህንነት ስጋት እንዲሁም የኮንቴነር ጭነት መጓተት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ኮንቴነር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ተሽከርካሪዎች ስንዴና የምግብ ዘይት በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አማካኝነት እየተጓጓዙ መሆኑን አቶ ፍስሐ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የጭነት ወጪን በመቀነስ ለተለያዩ ተቋማት ውጤታማ አገልግሎት እያቀረበ ነው ያሉት አቶ ፍስሐ፤ የባቡር መስመሩ ኢትዮጵያና ጅቡቲን በማገናኘት ከወደብ ወደ መሐል ሀገር የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን በማጓጓዝ ለትራንስፖርት ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቱ በድሬዳዋ፣ በሞጆ፣ በአዳማ፣ በለቡ፣ በእንዶዴ፣ በዲኬና በመኢሶ እንዲሁም በደወሌ የባቡር ጣቢያ መስመሮች የጭነትና የመንገደኞች የባቡር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ነው አቶ ፍስሐ የገለጹት፡፡
አቶ ፍስሐ እንዳመለከቱት፤ የባቡር መስመሩ በ20 ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በቀጣይም አገልግሎት መስጫ አዳዲስ ጣቢያዎችን ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የባቡር መሠረተ ልማቶች ስርቆት እና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ እንዲሁም የፀጥታ ችግር እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋና እና ፈታኝ ችግሮች መሆናቸውን አቶ ፍስሐ ተናግረዋል ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
