


መስኖ ማለት የገፀ-ምድር ወይም የከርሰ ምድር ውኃን በሰው ሰራሽ መንገድ በባህላዊ ወይም ዘመናዊ አሠራር በመጠቀም ወደ እርሻ መሬት በማድረስ ዝናብ ሳይጠበቅ ሰብልን ፣ የጓሮ አትክልትን ወይም ፍራፍሬ ተክሎችን የማልማት መንገድ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚዘረዝሩት ከሆነና በተግባርም እንደተረጋገጠው መስኖ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በተለይ በረሃማ በሆኑ አካባቢዎችና የዝናብ እጥረት በሚኖርባቸው ወቅቶች የመስኖ ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው፡፡ የመስኖ ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከማገልገሉም የእንስሳት መኖ በማልማትና የአከባቢውን ልምላሜ በመጠበቅ የአከባቢውን የአየር ፀባይ ሚዛንን ይጠብቃል፡፡
በግብርና ሜካናይዜሽን የመስኖ ልማትን በማስፋፋት የአካባቢያዊ ስነ-ምህዳራዊ ቀጠና መሰረት ያደረገ የእርሻ ልማት ስራ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው መንገድ እንዲደግፍ እንደ ቅድመ ሁኔታ ከሚቀርቡ ነገሮች አንዱ ዘመናዊ የመስኖ አውታር ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሀገራችን ኢትዮጵያ በመስኖ መልማት የሚችል 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አለ። ኢትዮጵያ የግብርና ምርቷን በማሳደግ ሕዝቦቿን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችላት አቅጣጫዎችን አስቀምጣ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ይህ በግብርናው የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚደረገው ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል።
በሀገራችን ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የመስኖ ልማት ሥራዎች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው ባይሆኑም በምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ ተብላ የምትጠራው ኢትዮጵያ ከመስኖ ልማት መጠቀም ባለባት ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅማለች ለማለት ግን አያስደፍርም። ይህንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ዘመናዊና ሳይንሳዊ የመስኖ አጠቃቀሞችን ተግባራዊ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡
ከ85 በመቶ ያላነሱ የሀገራችን ህዝቦች የሚተዳደሩት በግብርናው ዘርፍ መሆኑ ለመስኖ ዘርፍ ልዩ ትኩረትን ሰጥተን መስራት እንዳለብን ያሳየናል፡፡ እንደ ሀገር ለመስኖ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠት ተጨማሪ ስንዴ ከውጭ ሀገራት እንዳንገዛና ምርታማነታችንን ለማሻሻል የመስኖ ልማት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅተው ወደ ተግባር መገባቱ ይታወሳል። ከዚህ አንጻር ሀገራችን ያላት በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት በተገቢው በማልማት አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ከድህነት ለማላቀቅ፤ ስራአጥ ዜጎችን ወደ ስራ ለማሰማራት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ይገኛል፡፡
ሀገሪቱ ካላት በመስኖ መልማት ከሚችል መሬት በመቶኛ ሲሰላ እስከ አሁን መጠቀም የተቻለው ከ20 ከመቶ በላይ እንዳልደረሰ መረጃዎች የሚያሳዩ ስሆን በዘርፉ በበቂ መጠን የሰለጠነ የሰው ሀይል አለመኖሩ እና የመስኖ አውታሮች ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቀው ወደ ስራ ለመግባት ከተገቢው ጊዜ በላይ መውሰዳቸው ዋነኞቹ ችግሮች ናቸው፡፡
በክልላችንም በመስኖ ልለማ የሚችል ሰፊ መሬትና የውሃ አማራጮች የሚገኙበት ቢሆንም እስካሁን ድረስ የተገነባው የመስኖ አውታር ከፖቴንሻሉ አንፃር ሲታይ አንድ ከመቶ ያልደረሰ ሲሆን ከአገራዊ ሽፋንም በእጅጉ ዝቅ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡ በመሆኑም የክልላችን በመስኖ የመልማት ፖቴንሻልን ታሳቢ ያደረገ እና የመስኖ ልማት ሽፋኑን ከአገራዊው ሽፋን ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማደረግ የአነስተኛ መካከለኛና ሰፋፊ መስኖ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራዎች እና እንዲሁም የግንባታ ሥራዎች በክልሉ መንግስትና በፌደራል መንግስት ልዩ ትኩሬት ተሰጥቶ እየተመራ ይገኛል፡፡
በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግሮች ከመቀነስ አንጻር በሁሉም የግብርና ልማት መስኮች ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ማሰማራት ትኩረት የሚሻ ስሆን በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በክልሉ ከ2 ሺህ የሚልቁ ስራ አጥ ወጣቶችን በጊዜያዊነት በአካባቢያቸው በመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታና ተያያዥ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ በማድረግ ስራ አጥነትን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እንጂነር አሸናፊ ሽብሬ ይህም ስራ አጥነትን ከመቅረፍ በሻገር የተለያዩ የግንባታ ሥራ ሙያን ልምድ እንዲቀስሙና የዕውቀት ሽግግርም እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል ፡፡



በተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ በየዓመቱ አንድ የውኃ ባንክ እንዲኖረው የሚያደርጉ አማራጮች በሰፊው እንዲሰሩ ርብርቦች ማድረግ እንደሚያሻ የገለጹት ኃላፊው በዚህ መሠረት አብዛኛው ቤተሰብ የውኃ ባንክ እንዲኖረው ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ በግብርናው እና በውሃው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት እጅና ጓንት ሆነው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው እንጂነር አሸናፊ ያስገነዘቡት።

በክልሉ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት የግብርናው ዘርፍ ለማጠናከር መንግሥት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ አዲስና ነበር የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ወደ ልማት እንዲገቡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በመስኖ ልማት ስራ በምግብ ሰብል ምርት ራስን ከመቻል ባለፈ ዘርፉን ማዘመንና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም ተጨማሪ ምርቶችንና ገቢ ለማግኘት በዋነኝነት የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በአግባቡ መሰጠቱም ዘመናዊ፤ ሳይንሳዊና ውጤታማ የመስኖ ልማት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ በያዝነዉ ግማሸ በጀት ዓመት የመስኖ አውታር ጥናትና ዲዛይን ሥራዎችን በተመለከተ መስኖ ልማት ጥናትና ዲዛይን የተካሄደ አጠቃላይ መሬት መጠን ከ 22,120 ሄ/ር ወደ 29,430 ሄ/ር ለማሰደግ በዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ ፕሮግራም በጀት የሰባት መካከለኛና ከፍተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ሥራ በማከናዎን ከእነዚህ መካከል የአራት መስኖ ፕሮጀክቶችን (ጊንድራ፣ ኡማ ፣ ሁምበች እና ዎጋዬ) ጥናትና ዲዛይን ሥራ በአማካይ ከነበረበት 62.25% ወደ 79% ለማድረስ ታቅዶ 77.5 (91%) ላይ ሲገኝ የቀሪ 3 ፕሮጀክቶች (ኦይቢ፣ ቱም እና ካሹ ) የጥናትና ዲዛይን ሥራን ከነበረበት 38% ወደ 55% ለማድረስ ታቅዶ 48.33% ላይ ይገኛል፡፡
ከመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ አኳያ የመስኖ አውታሮች ግንባታ ሽፋንን ከ 2,933.99 ወደ 3975.78 ሄ/ር ለማሳደግ ታቅዶ በዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ ፕሮግራም ስምንት የመስኖ ፕሮጀክቶች ( ቡኒ ፣ ዳማ፤ ቡቢ፤ ኦልሙ፤ ፅልቤ፤ ውኒ ፣ ሻታ እና ዋርዋሮ) ፣ በግብርና ዕድገት ፕሮግራም ሦስት ፕሮጀክቶች (ማራጫ ፣ ኦፊያ ፣እና ፔቱ ) ፣ በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ሦስት የመስኖ ፕሮጀክቶች (ሽመሮ ፣ ጋሺ እና ማጋ) ፣በተሳትፎአዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም የቶኒ መስኖ ፕሮጀክት ፣ በባለአነስተኛ ይዞታ መስኖ ልማት ፕሮግራም የቄነች መስኖ ፕሮጀክት እና በቆላማ አከባቢ ልማት ፕሮግራም የኪሉ መስኖ ፕሮጀክት በድምሩ 1,613.38 ሄ/ር መሬት ማልማት የሚያስችሉና 1,504 አ/አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 17 መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራን በማከናዎን ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል በበጀት ዓመቱ የ8 መስኖ ፕሮጀክቶችን (ቡኒ፤ቶኒ፣ ቄነች ፣ ማራጫ ፣ ኦፊያ ፣ ፔቱ ፣ ሻታ እና ዋርዋሮ) የግንባታ ሥራ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
የ6 ፕሮጀክቶችን (ዳማ፤ ቡቢ፤ ኦልሙ፤ ፅልቤ፤ ውኒ እና ኪሉ) አፈፃፀማቸው በአማካይ 46.33% የተከናወነ ሲሆን ሌሎች ሦስት ፕሮጀክቶች (ሽመሮ ፣ ጋሺ እና ማጋ) ወደ ግንባታ ሂደት ለማስገበት ለጨረታ ሂደት የዶኩሜንት ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል፡፡



በዘላቂ የልማት ግቦች ማሳኪያ ፕሮግራም፣ በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በጀት እና በህብረተሰብ ተሳትፎ 90 ሄ/ር መሬት በማልማት 81 አ/አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሦስት አነስተኛ መስኖ ተቋማት ጥገናና መልሶ ግንባታ ስራ ለማከናወን የሚያስችል የዲዛይን ማሻሻያና ሌሎች የዝግጅት ስራዎች በተቋሙ እየተከናወኑ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡
በክልሉ የመስኖ ዉሃ ተጠቃሚ ማህበረሰብ ቁጥር 3890 የደረሰ መሆኑ የተገለጸ ስሆን የመስኖ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የማላመድ፣ የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች የግንዛቤ ማሳደግያና ሌሎች ሥራዎች በተጠቃሚዉ ህብረተሰብ ላይ እየተከናወነ እንደሚገኝና በ79 ነባር የመስኖ ዉሃ ተጠቃሚዎች ማህበራት ላይ የማጠናከሪያ ስራ መሰራቱ ተነግሯል።
በዘርፉ ከሚገጥሙ ተግዳሮቶች አንዱ የውሃ መሳቢያ ፓምፒ አጠቃቀምና ጥገና ችግር በመሆኑ ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ የውሃ ስራዎች ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የኤሌክትሮኒክስ መሀንዲሶችን በማሰልጠን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንዳለም ተጠቁሟል።
የክልሉን አርሶናአርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የተጀመረው የዘመናዊ መስኖ ግንባታ አውንታዊ ውጤት እያስመዘገም ይገኛል። በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች በመስኖ የለሙ የበጋ ስንዴ፣ የጓሮ አትክልት ማሳ መመልከት አሁን አሁን የተለመደ ሆኗል።



የተገነቡ የመስኖ አውታሮች በደለል እንዳይሞሉና በግንባታውም ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተጠቃሚ አርሶና አርብቶአደሮች የተጠናከረ ክትትል ይቀጥል መልዕክታችን ነው።
አዘጋጅ: ዕድገቱ በዛብህ
