


በአማራ ክልል የልማት ሥራዎች ዙሪያ የሚመክር የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በምክክር ሂደቱ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ እና ሌሎችም የፌዴራል መንግሥት አመራሮች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ወደ ክልሉ ለመጡ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
የፌዴራል እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በጋራ ተገናኝተው መምከራቸው የክልሉ ሕዝብ የሚፈልጋቸውን ልማቶች ለመለየት እና በቅንጅት ለመሥራት ዕድል እንደሚሰጥም ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ድጋፍ ለማድረግም ያግዛል ብለዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “ሰላም እና ልማት የተሳሰሩ ነገሮች ናቸው፤ አንዱ ያለሌላው ሊሳካ አይችልም” ብለዋል።
ሰላምን እያስከበሩ ልማትን በትኩረት ማካሄድ ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ልማት ያለ ሰላም፣ ሰላምም ያለ ልማት የሰመረ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ እና ሕዝቡ የተሟላ ሰላም እንዲያገኝ ሕግ የማስከበር ሥራ በተሟላ ሁኔታ እንዲከናወን ይሠራልም ብለዋል።
የዛሬው ውይይት የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ ሕዝብን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ሥራዎችም ዙሪያ በመነጋገር መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነውም ብለዋል።
