




በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አተገባበርን ለማሻሻል የሚመክር መድረክ በታርጫ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል ።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማ አምራች እና ጤናማ ማህበረሰብ የመገንባት ሂደት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው የጤና ተቋማት አገልግሎት እና አደረጃጀት ሲገነባ ነው።
ስለሆነም በክልሉ በየደረጃ የሚገኙ የመንግስት መዋቅሮችና አደረጃጀቶች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች የዘርፉን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በተለይም በጤና ኬላ ደረጃ እየተሰጡ ባሉ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ላይ እምርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
ለዚሁ ለውጥ በተለይም የሴቶች ልማት ቡደንና የ 1ለ 5 ትስስሮች አስተዋጽኦ የላቀ ነውም ብለዋል።
ሆኖም ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሴቶች ልማት ቡድኖችና ትስስሮች ምዘና ጉድለት፣ የክትትልና ድጋፍ ውስንነቶች እንዲሁም በፓኬጆች አፈጻጸም ላይ መቀዛቀዞች መታየታቸውን አቶ ኢብራሂም ጠቅሰዋል።
በዚሁ ሳቢያ የወባ ወረርሽኝ መጨመር፣ የህጻናት ዕድገት ክትትልና የጨቅላዎች ህክምና ማነስ እንዲሁም የመፀዳጃ ቤት ግንባታና አጠቃቀም ላይ ጉድለቶች ተስተውለዋል።
የተግባራት አፈጻጸም በአንዳንድ አካባቢዎች በነበረበት መቆየት እንዲሁም በአንዳንዶቹ ወደ ኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች መታየታቸውን ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው ክትትል ማረጋገጡንም አስረድተዋል ።
እንደ ኃላፊው ገለጻ እነዚሁ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል በቀጣይ 15 ዓመታት የሚተገበር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር አየተገባ ይገኛል።
በመድረኩ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉት ወቅት ለሁሉም መሠረት የሆነው የጤናን ሥራ ከመደገፍ ረገድ ተግባራዊ ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል ።
እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ በዘርፉ ከጤና ኬላ ጀምሮ እየታዩ ያሉ ለውጦችን አጠናክሮ የማስቀጠል ብሎም በስፋት የሚታዩ ውስንነቶችን ከማስተካከል ረገድ ቅንጅታዊ ሥራ ያስፈልጋል ።
ጉባዔውም በእስካሁኑ የፕሮግራሙ አፈጻጸም የተገኙ ውጤቶችን፣ የታዩ ድክመቶችንና መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ መክሮ ለቀጣዩ ተግባር አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎም ይጠበቃል።
በምክክሩ በዳውሮ እና ኮንታ ዞኖች ያሉ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ፣ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሳትፈዋል ሲል ከዳውሮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
