የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ከኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የትብብር ስነድ ተፈራረመ

Spread the love

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል መንግሥት፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል የጋራ ውይይት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾና የክልሉ የካቢኔ አባላት በተገኙበት አድርገዋል።

በሁለቱ አጎራባች ክልሎች ለዘመናት የዘለቀው ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲሁም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዳለ ያወሱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ይህን መልካም ግኑኝነት ወደ ልማት ስራዎች ለማሳደግ የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በክልሉ ያለውን የልማት ክፍተትና ፍላጎት በመለየት የኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በትብብርና በጋራ ለመስራት የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ በክልሉ ሁለንተናዊ ልማት ያፋጥናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በማዕድን፣ በግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር እንዲሁም በኮንትራት አስተዳደር የነበራቸው ልምድ በማካፈል ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል።

የልማት ድርጅቱ በሀገር ውስጥ ከሌሎች ክልሎች ጋር አብሮ እየሰራ እንደሆነና ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ በጅቡቲ እና ሩዋንዳ በግንባታ ዲዛይንና ቁጥር እየሰራ እንደሚገኝም የተገለጸ ሲሆን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የልማት አቅሞችና በቀጣይ ከልማት ድርጅቶቹ ጋር ተቀናጅተው መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የክልሉ ዉሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸዉ በኩል ገለጻ ተደርጓል።

የኦሮሚያ ክልል ከአጎራባች ክልሎች ጋር በቅንጅትና በትብብር በመስራት ያምናሉ ያሉት የኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢና የክልሉ ፕሬዝዳንት የፕሮጀክቶች አማካሪ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ የተፈራረመው ስምምነት የሁለቱ ክልሎችን ሁለንተናዊ ግኑኝነት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እንደሆነ ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልሉ የካቢኔ አባላት እንዲሁም የኦሮሚያ የልማት ድርጅቶች ስራ-አስፈፃሚዎች ተገኝተዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *