
የ24 ዓመቱ የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ኬንያዊው አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም በመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የዓለም አትሌቲክስ አስታወቀ።
ኪፕቱም ባለፈው ጥቅምት ወር ቺካጎ ውስጥ በተደረገ የማራቶን ውድድር 2:00:35 በሆነ ሰዓት በመግባት የዓለም ክብረ ወሰን መስበሩ ይታወሳል።
ይኸው ክብረ ወሰን ባለፈው ሳምንት መጽደቁም ይታወቃል።
አትሌቱ እና ሩዋንዳዊ አሠልጣኙ ጌርቫይስ ሐኪዚማና ሕይወታቸው ያለፈው ኤልዶሬት ካፕታጋት በተባለ መንገድ ላይ መሆኑን የሀገሪቱ ትራፊክ ፖሊስ ገልጿል።
አትሌት ኪፕቱም በመጪው ሚያዚያ ወር በሮተርዳም በሚካሄድ የማራቶን ውድድር ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት አቅዶ እየሠራ እንደነበርም ተጠቁሟል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
