



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ
በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አፈጻጸም እና ወረርሽኝ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ያደረገ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የድጋፍ ስራ ለሚሰሩ የቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች ኦሬንቴሽን ሲሰጡ እንደገለጹት የጤና ኤከስቴንሽን ፕሮግራም አተገባበርን በማጠናከር እና ስራው በተቀጣጠለ አኳን እንዲሰራ በክልሉ በሶስት ክላስተር ከተሞች የጤና ኤከስቴንሽን ባለሙያዎች ግምገማ ነክ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸው አስታዉሰዉ ከስልጠና በኋላ በጤና ኤከስቴንሽን ፕሮግራም በውይይቱ በተግባባናቸው እና በቀጣይ ቀሪ ወራት ከተቀመጡ ግቦች አንፃር የመጡ ለውጦች እና ማነቆዎችን ለይቶ በመደገፍ ዉጤታማ ስራ እንዲሰራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ከድጋፍ ቡድኑ አባላት ይጠበቃል ብለዋል።
የመድሃኒትና የግብአት እጥረት ለማቃለል መንግስት የሚልኳቸው ግብአቶችና መድሃኒቶች ብክነት እንዳይገጥሟቸው የተዘረጉ የአሰራር ስርአት በተገቢው መፈፀማቸው በድጋፋዊ ክትትል እስከ ጤና ኬላ ድረስ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል አቶ ኢብራሂም።
ለተገልጋዮች የተሳለጠ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል የጤና ጣቢያና የጤና ኬላዎች ትስስር ወሳኝ በመሆኑ ይህንን አገልግሎት አሰጣጥ ለማጠናከር የተዘረጉ የአሰራር ስርዓቶች መፈተሽ ይገባል ብለዋል።
መጭው የክረምት ወራትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል እየተወሰደ ያለው የመከላከል ስራም እንደሚገመገም ጠቅሰዋል።
በመጪዉ ክረምት ወራት የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል 79,590 ቤቶችን መርጨት የሚያስችል ከሚካል እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን እስከ ቀበሌ ድረስ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ በመስራት ለተግባሩ በየደረጃው የሚገኝ አመራር እና ባለሙያ ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ሌሎች ተላላፊና ተላላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል የአሰራር ስርዓቶች መዘርጋታቸው በማረጋገጥ ግብረመልስ ሊሰጥ እንደሚገባ አቶ ኢብራሂም አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል።
ድጋፉ በስድስቱም ዞኖች እስከ ጤና ኬላዎች ድረስ የሚደረግ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
