በሣይለም ወረዳ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የካፋ ዞን አስተዳደር አሳሰበ

Spread the love

በካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በአቶ እንዳሻው ከበደና በዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በአቶ አጥናፉ ሀይሌ የተመራ የዞን ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በወረዳው የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።

በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰራ ያለው ከኤምርኪ አጋሮ ሰባት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እና በኤምርኪ ቀበሌ በአርሶ-አደር ማሰልጠኛ ማዕከል አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም እየለማ ያለው የስንዴ ማሳ ተጎብኝተዋል።

በማሻሚ ማዘጋጃ በፌደራል መንግስት የሚገነባውና ለ5 መቶ አባወራዎች አገልግሎት የሚሰጥ የፀሀይ ሀይል ማመንጫ ግንባታ የተጎበኘ ሲሆን ፤ 4 ሺህ 700 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ መሆኑ ተገልጿል።

የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከማል ጠይብ ወረዳው እንደ ሀገር በጤና ዘርፍ ግንባር ቀደም መሆኑን ተናግረው ፤ 18ቱ የጤና ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ማቆያዎችን የማጠናከር ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጤና መሰረተ-ልማቶችን ለማስፋትና ለህብረተሰቡ በአቅራቢያው አገልግሎት እንዲያገኝ በፌደራል መንግስት 47 ሚሊዮን ብር ወጪ በኤምርኪ ቀበሌ ሁለተኛ ትውልድ ጤና ጣቢያ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

የወረዳው ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሞ መንገሻ በበኩላቸው ፤ እንደ ወረዳ 28 የአርሶ-አደር ማሰልጠኛዎች እንዳሉ በመግለፅ እነዚህንም ሞዴል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ወረዳው ያለው አፈር በከፍተኛ ሁኔታ በአሲድ የተጠቃ በመሆኑ ፤ ዘንድሮ 3 መቶ 30 ኩንታል ኖራ በማቅረብ አፈርን የማከም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አየለ በሁሉም ዘርፎች ህብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የአርሶ-አደር ማሰልጠኛ ማዕከላትን ሞዴል የማድረግ ስራ እየተጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንገድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ከጬሌ ሼካ ቀጀታ መንገድ ስድስት ቀበሌዎችን የሚያገናኝና 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ፤ የጉብኝቱ አካል ሆኖ ስራው ተገምግሟል።

ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ቡና የሚመረትበት አካባቢ በመሆኑ መንገዱ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል ።

2013 ዓመተ-ምህረት ላይ ጥገናው የተጀመረ ሲሆን ፤ ዘንድሮ ለመጨረስ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት አስተዳዳሪው ለግንባታው ከህብረተሰቡ 3.5 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል።

የመንገድ ስራ በመንግሥት ብቻ የማይዳረስ በመሆኑ ፤ ህብረተሰቡን በማስተባበር እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ተናግረዋል።

“አንድ መንገድ ለአንድ ወረዳ” በሚል መርህ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ፤ ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰራ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

ከጬሌ ሼካ ቀጀታ ያለው መንገድ በበጋ ወራት እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ አሁን የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት አቶ እንዳሻው አመራሩም በአግባቡ ስራ ላይ እንዲያውል አሳስበዋል።

በግብርና ዘርፍ በአርሶ-አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚታየው የልማት እንቅስቃሴ አስደሳች ስለሆነ ወደ አርሶ-አደሩ ማሳ ማስፋፋት ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዘበዋል።

በጉብኝቱ ላይ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደን ጨምሮ የካፋ ዞን እና የሣይለም ወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል ሲል ቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *