




የሰቆጣ ቃልኪዳን ውጤታማነት ለማሳደግ ተደራሽነቱን ለማስፋት በትኩረት መስራት እንደሚገባ የምግብ ስርዓትና ኒውትሪሽን ጥምር የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴር በጋራ የሚያስተባብሩት የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ተካሂዷል።
ውይይቱ በኮሚቴው ስር የሚገኙ 15 ሴክተር መስሪያ ቤቶችን ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አላማ ያደረገ ነው።
በሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንና ኒውትሪሽን ሴክሬተሪያት የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ውጤት እና ለውጥ ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ የተገኘውን ተሞክሮ ወደ ሌሎችም በማስፋት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በሰቆጣ ቃልኪዳን፣ በምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንና በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት የተከናወኑ ስራዎችና የተገኙ ስኬቶች አበረታች ናቸው ብለዋል።
አሁንም በርካታ የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ለበለጠ ውጤታማነት መስራት አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
