በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2017 ዓ.ም

Spread the love

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በይፋ ተጀመረ

የ2017 ምርት ዘመን ክልላዊ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ማብሰሪያ ፕሮግራም በካፋ ዞን፣ ሺሾ እንዴ ወረዳ፣ ዳኼራ ቀበሌ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት በይፋ ተከናውኗል።

መርሐ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድ የኢኮኖሚና መሰረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ ዶ/ር ኢንጂነር ምትኩ በድሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የሚቃወቅ መሆኑን በማንሳት የተፋሰስ ልማት ስራው ይህንን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ከክልሉ ምሥረታ ወዲህ በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊው ዘላቂነትን በማረጋገጥ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተፋሰስ ልማት ስራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ምትኩ አክለው በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ለቀጣይ 45 ቀናት በሚከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ በመውጣት ንዑስ ተፋሰስ እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ አማካሪና የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዩሐንስ መላኩ በበኩላቸው በክልሉ በ2017 የተቀናጀ ተፋሰስ 225ሺህ ሄክታር መሬት በ1ሺህ 100 ንዑስ ተፋሰሶች ስር እንደሚለማ በመገለጽ በዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ሌሎች የግብርና ልማት ስራዎችን ከተፋሰስ ልማት ስራው ጊር አቀናጅተው መምራት እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ዩሐንስ የዘንድሮውን የተፋሰስ ልማት ስራው በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ለማስፈጸም በቂ ቅደመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳደርና ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሥ በበኩላቸው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ እንደሚረዳ በመግለጽ ከዚህ ቀደመ በለሙ ተፋሰሶች አርሶአደሮች የስነ ህይወታዊ ተከላ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ እያገኘ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተፋሰስ ልማት ስራው የተፈጥሮ ሀብት በማሻሻል የውሃ ሀብቶችን ጠብቆ ለማቆየትም እንደሚረዳ የጠቆሙት አቶ ደመላሽ የሚለሙ ተፋሰሶች ዘላቂነት ለማረጋገጥ የስነ ህይወታዊ ስራዎች በተላይም በመኖ ልማት ላይ አርሶአደሩ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

አቶ ደመላሽ አክለው ሌሎች የልማት ስራዎችን ከተፋሰስ ልማት ተግባር ጋር በማቀናጀት ማስቀጠል እንደሚገባ በማሳሰብ በሚቀጥሉት የትግበራ ጊዜያት በዞኑ ሁሉም አከባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለመደ መልኩ በተፋሰስ ልማት ስራው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት የካፋ ዞን ግብርናና አከባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዋ አባመጫ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአፈር ጤንነት በመጠበቅ የግብርና ምርት ውጤታማነት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

በማብሰሪያው ፕሮግራም የተገኙ አርሶአደሮች በበኩላቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በአከባቢው የተለመደ ተግባር በመሆኑ በልዩ ትኩረት የሚፈጸም እንደሆነ በማንሳት ተግባሩን አጠናክረው ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *