በቤንች ሸኮ ዞን ዞናዊ የተፋሰስ ልማት ስራ በሁሉም መዋቅሮች ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እየተሰራ ነው

Spread the love

የክልል ፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሼይ ቤንች ወረዳ ማዝ ቀበሌ ሺንክ ንዑስ ተፋሰስ በይፋ ተጀምሯል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ የተፋሰስ ልማቱን በይፋ ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት የአፈር ሀብታችንን መጠበቅ ሰውን ፣ እንስሳትንና የውሀ ሀብታችንን መጠበቅ በመሆኑ ዘንድሮ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተፋሰስ ልማት ለበርካታ አመታት እየተሰራ የቆየና በህዝቡ ውስጥ ባህል ሆኖ የቆየ ተግባር መሆኑን ገልጸው ዘንድሮ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያ ጠቀሜታ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች ፣ የመኖ ሳርና መሰል ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል።

የዞኑ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ እንደተናገሩት በዞኑ በ96 ንዑስ ተፋሰሶች 34ሺ 480 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ይሰራል ብለዋል። የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራችንን መስራት የአፈር ለምነትን በማስጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

የሼይ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ኒሳብ እንደተናገሩት በወረዳው በ28 ቀበሌዎች ከ7ሺ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ይሰራል ብለዋል። ለተግባሩ ከ54ሺ በላይ ሰዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አትርሴ ኃይሌ እንደተናገሩት በማዝ ቀበሌ ብቻ ከ250 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የስነ ህይወታዊና ስነ አካላዊ ስራ ይሰራል ብለዋል። ባለፉት አመታት በወረዳው በተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራ የተራቆቱ መሬቶች አረንጓዴ ለብሰዋል ፣ የጠፉ የውሀ አካላትም ማገገማቸውን ገልጸዋል።

በተፋሰስ ልማቱ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ግለሰቦች እንደተናገሩት ተፋሰስ ልማት የአፈር ለምነትን ከመጨመሩ ባሻገር ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር እንዳገዛቸው ገልጸዋል። ዘንድሮም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ሙዝ ፣ ሸንኮራ የመሳሰሉ ተክሎችን እየተከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መድረኩ የክልል ፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *