የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት አፈር እንዳይሸረሽርና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለፀ

Spread the love

” የአፈር ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል ከጥር 22 /2017ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 45 ቀናት የሚደረገው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ማስጀመሪያ መርሃግብር በሸካ ዞን የኪ ወረዳ ዝንኪ ቀበሌ ተካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ከጁአብ እንደገለጹት የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ስራው እንደ ክልል በዚህ አመት 2 መቶ 25 ሺህ ሄክታር መሬት የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው በተፋሰስ ስራው 9 መቶ 96 ንዑስ እና 1 ሚሊየን 15 ሺህ 3 መቶ 12 የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

መሬት ከሀብቶች ሁሉ የላቀ ሀብት ነው ያሉት ኃላፊው የመሬት ሀብታችንን በትኩረት በመያዝ ብልጽግናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል።

በዞኑ የአብዛኛው አርሶ አደር ቡና ያረጀና ምርታማነቱም ዝቅተኛ በመሆኑና የቡና ዝርያው በውል የማይታወቅ በመሆኑ በዘመናዊና ምርታማ በሆነ የቡና ዝርያ ለመተካት ሰፊ ስራ እንደሚሰራ ተናግሯል።

የሸካ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የውሃ ማዕድን ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ በላቸው ጋራ በማስጀመሪያ መርሃግብር ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ያላት ብቸኛ ሀብት የሰው ኃይል ውሃና አፈር በመሆኑ አቀናጅቶ መምራት ለነገ ሀብት ብቸኛ አማራጭ ነው ብለዋል።

የሸካ ዞን ግብርና ደን አካባቢ ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሳልኝ እንደገለፁት በዞኑ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን እና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ስላለው ተግባሩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።

በሸካ ዞን በዚህ አመት 17 ሺህ 9መቶ 13 ሄክታር መሬት የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው በተፋሰስ ስራው 59 ንዑስ እና 1 60 ሺህ 5 መቶ 9 የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል

በዞናችን ከፍተኛ የቡና ሽፋን ያለው መሆኑን አስታውሰው ነገር ግን የጥራት ደረጃው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ ይህን ችግር ለመፍታት በዚህ ተፋሰስ የጉንደላና ነቀላ ስራው በኩታ ገጠም በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ተሰማ በተፋሰስ ልማት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ገልፀው በቡና ነቀላና ጉንደላ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

መንግስት ለተፋሰስ ልማት ስራው ልዩ ትኩረት በመስጠትና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።

በተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የክልል፣የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት፣ የቀበሌው የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን በተፋሰስ ስራው ከቡና ነቀላና ጉንደላ ባሻገር ሌሎች በርካታ ተግባራት እንደሚሰሩም ተገልጿል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *