



ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እውን የሚያደርግ አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን የፓርቲው አመራሮች ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በፓርቲው የመጀመሪያው ጉባኤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገት የሚያፋጥኑ ተግባራትን ለማከናወን ቃል መገባቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን በማሳለፍም ለተግባራዊነቱ በስፋት መስራት ተችሏል።
በዚህም የተባበረ ጥረት ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እውን የሚያደርግ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ስኬት ማስመዝገቡን የፓርቲው አባላትና አመራሮች ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር)፤ መንግስት ብልጽግናን ለማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በርካታ እርምጃዎች መውሰዱን ተናግረዋል።
የዴሞክራሲ ምህዳሩን ከማስፋት ባለፈ ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም በመላው ሀገሪቱ ምክክር እንዲካሄድ እና የውይይት ባህል እንዲዳበር እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
በፓኪስታን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር፤ ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች በመተግበር ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ለውጡን ከማጽናት ጀምሮ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው ወንድማማችነት እና አብሮነት የጎለበተባት ሀገር እየተገነባች መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ተሰሚነት እና በቀጣናው ያላትን ተጽእኖ ፈጣሪነት የሚያሳድጉ ስራዎች መሰራታቸውንም ነው የገለጹት።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር)፤ ብልጽግና ሁሉም እኩል የሚሳተፍበትን መብት በተግባር ማረጋገጡን ተናግረዋል።
አካታችነትንና ብዝሃነትን በማረጋገጥ ረገድ አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢፍቱ አህመድ፤ ብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛ ጉባኤው የተጀመሩትን ስራዎች የሚያጸኑ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
