በኮንታ ዞን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራ በይፋ ተጀመረ።

Spread the love

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች የተገኙ ተሞክሮዎችን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በተቀናጀ መንገድ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።

በዞኑ የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ “የአፈር ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ሀሳብ በአመያ ከተማ አስተዳደር ጨካ ቦቻ ቀበሌ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ም/ል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ወጁ የተፋሰስ ልማት ስራ የመሬት ለምነት ተጠብቆ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ እና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል መሆኑን በመረዳት በሁሉም አካባቢ ህብረተሰቡ በነቂስ እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህን ለማጠናከር በተቀናጀ መልክ ሊመራ እንደሚገባ ገልፀው ከዚህ ተግባር ጎን ለጎን የበልግ እርሻ እና ሌሎች ወቅታዊ ተግባራት ተያይዘው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዞኑ ግብርና አካ/ጥ/ህ/ስራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማስረሻ ሀደሮ በበኩላቸው በዞኑ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቡን አብራርተዋል።

በዘንድሮ ተፋሰስ ልማት ስራ በ73 ንዑስ ተፋሰሶች 32,248 ሄ/ር መሬት እንደሚለማ የጠቆሙት ኃላፊው ከ57 ሺህ በላይ የሰው ኃይል ተሳታፊ እንደሚሆን በማንሳት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ለሚቀጥሉት 30 ቀናት እንደሚተገበርና በቀጣይ 15 ቀናት የስነ-አካላዊ ስራዎች እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

የአመያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተመስገን ደጀኔ ቀደም ሲል በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ተግባሩ በዞኑ ብሎም በከተማ አስተዳደሩ ባህል እየሆነ መምጣቱን ገልፀው በተግባሩ የጉልበት ብክነት እንዳይኖር በተደራጀ ሊመራ ይገባል ብለዋል።

ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ዳማሳ ደምሴ እና ወ/ሮ አለሚቱ አንዳሼ የተፋሰስ ስራን በትኩረት በመስራታችን ዛሬ ለእርሻ መሬትና ለከብት ሳር ማግኘታቸውን ተናግረው ውጤቱን ለማስቀጠል ልምዳቸውን ተጠቅመው እየሰሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ጥቅሙ የእኛው በመሆኑ ዘንድሮም አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል ሲል የዘገበው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *