የብሔራዊነት ገዥ ትርክትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ይሰራል – የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች

Spread the love

የብሔራዊነት ገዥ ትርክት የመፍጠርና የሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር የተጀመሩ ሥራዎችን በትጋት እንደሚያስቀጥሉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ከጥር 23-25/2017 ዓ.ም ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ባወጣው የአቋም መግለጫ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲሳካ ነጣጣይ ትርክቶች ተሸንፈው አስተሣሣሪ ትርክቶች የበላይነት ማግኘት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡

የብሔራዊነት ገዥ ትርክት በልሂቃን እና በሕዝቡ ዘንድ እንዲሰርጽና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር በስፋት እንደሚሰራም ነው በአቋም መግለጫው የተመላከተው፡፡

ይህንን የበለጠ ለማሳካትም በመጪው ጊዜያት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና በሁሉም የአማራጭ መንገዶች በማኅበረሰቡ መካከል መግባባትን የሚፈጥሩ ሕዝባዊ ውይይቶች እንደሚከናወኑም ነው ያረጋገጠው፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በፓርቲው የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሁሴን፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ባህል ነጣጣይ ትርክትን በማስቀረት አሰባሳቢ ትርክት እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያውያንን አብሮነት በማጠናከር ረገድ የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል እና በፓርቲው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፥ ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ፓርቲው በአንደኛ ጉባኤው ለህዝብ ቃል በገባው መሰረት ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና የጋራ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራትን በስኬት ማከናወኑንም ጠቅሰዋል።

ፓርቲው በተለይም በመደመር እሳቤ አካታች የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ እና በሀገር ጉዳይ ሁሉም እኩል ተሳታፊ እንዲሆን ተግባራዊ እርምጃ መውሰዱ ሀገራዊ የፖለቲካ ስብራትን የጠገነ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ለማስረፅና በሕዝቦች መካከል ትሥሥርና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ብልፅግና ፓርቲ በመሪነት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስቡና ለጋራ ግብ የሚያነሳሱ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት፥ የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል እና በፓርቲው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው።

የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት ሕዝቡን በማሳተፍ ለገዥ ትርክት ግንባታ፣ ለአካታች የፖለቲካ ባህል መዳበር እና ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት በትጋት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *