የካፋ ብሔር‹‹ የቤነ ሻዴዬ ባሮ›› የዘመን መለወጫ በዓል ረጂም ዘመናትን ያስቆጠረ የተበታተኑትን ወደ አንድ ማዕከል ያሰባሰበ እንደሆነ የሚክረቾ አመራሮች ተናገሩ

Spread the love

የካፋ ብሔር ‹‹ የቤነ ሻዴዬ ባሮ›› የዘመን መለወጫ በዓል ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በየዓመቱ መስከረም ወር በገባ ከ10-13 ባሉት ቀናቶች የሚከበረው የካፋ ብሔር ‹‹ የቤነ ሻዴዬ ባሮ›› የዘመን መለወጫ በዓል ሶስት ስርዎ መንግስታትን ያሳለፈ የረጂም ጊዜ ታሪክ ያለው መሆኑን የካፋ ምክሬቾ አባል ጉጀራሻ አሰፋ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ጉጀራሻ አሰፋ በሰጡት መግለጫ በብሔሩ የቀን አቆጣጠር ለ750 ዓመታት ተከብሮ እንደነበርና በኋላም ነሐሴ 26/ 1889 ዓ/ም ወዲህ ለዓመታት በዓሉ ሳይከበር ተቋርጦ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ይህንን ለረጂም ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የብሔሩን የዘመን መለወጫ በዓል በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ እንደሚገኝ ጉጀራሻ አሰፋ አብራርተዋል፡፡

በካፋ ባህል አማካሪ ምክርቤት የህዝብ ግንኙነትና የአስተዳደር ክፍል ተጠሪ የሆኑት ሾደራሻ ተካልኝ ሽፈራው በበኩላቸው በምክሬቾ 12 ወራፎች መኖራቸውንና እነዚህ ወራፎች የዓመቱን አፈጻጸም ጥንካሬዎችና ድክመት በመገምገም ለቀጣይ ዓመት ዕቅድ በማዘጋጀት እንደሚከበር ያስረዳሉ፡፡

በበዓሉም የልማት ስራዎች የሚገመገሙበት፣ዘመኑ ያለፈበት ሁኔታ የሚዳሰስበት፣በኃላፊነት ላይ ያሉ የአመራርነት ስራዎቻቸው የሚፈተሽበትና በአፈጻጸሙ ድክመት ያሳየው ተሽሮ በምትኩ ሌላ የሚተካበት ስርዓት የሚንጸባረቅበት እንደሆነም ሾደራሻ ተካልኝ አስረድተዋል፡፡

በበዓሉም ህዝቡና ንጉሱ በዓመት አንዴ የሚገናኙበትና የሚመራረቁበት ፣የንጉሱን ትዕዛዝ በማክበር ህዝቡ እርሻውን የሚያርስበት እና ህዝቡን ደህንነት የሚያረጋግጡበት መሆኑን ሾደራሻ ተካልኝ አስረድተዋል፡፡

የዘንድሮው በዓል ከመስከረም 10-13/ 2016 በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እንደሚከበር ያስረዱት በባህላዊ አማካሪ ምክርቤት አመራር የሆኑት ዎተራሻ በየነ ዳኬጉቾ ተናግረዋል፡፡

ዎተራሻ በየነ አክለውም ክረምቱ አልፎ ብርሃን የሚገባበትና ቡቃያ የሚፈካበት ወቅት በመሆኑ በዓሉ በድምቀት ይከበራል ብለዋል ፡፡

በዓሉ በአካባቢ በመጠራራት ያለውን በመካፈልና በመቋደስ ፣የተቸገሩትን በመርዳት፣በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ተከብሮ እንደሚውልም ዎተራሻ በየነ ገልጸዋል ፡፡

የካፋ ብሔር‹‹ የቤነ ሻዴዬ ባሮ›› የዘመን መለወጫ በዓል ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝም ጊምበራሻ መለሰ መሸሻ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የምክረቾን ስርዓት የሚያንጸባርቁ ስራዎች መኖራቸው ፣የ18 ቱ ነገስታት መካነ መቃብር ጠሎ ወረዳ ሾሻሞጎ አካባቢ ያለውን ስርዓት የማጉላት እና በዘመኑ የነበሩ ቅርሶችን የማስተዋወቅና የንጉሱን በዘመኑ ይሰሩት የነበረውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀም ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝም ጊምበራሻ መለሰ ተናግረዋል፡፡

የካፋ ብሔር ‹‹ የቤነ ሻዴዬ ባሮ›› የዘመን መለወጫ በዓል ከዚህ ቀደም ማሽቃሮ ባሮ ተብሎ ከመስቀል በዓል ጋር አብሮ ይከበር የነበረው አሁን ላይ በካፋ ባህላዊ አማካሪ ምክርቤት ውሳኔ መሰረት ‹‹ የቤነ ናቶ›› የዘመን መለወጫ በዓል ሆኖ እንዲከበር መወሰኑንና ትርጓሜውም ህዝብ ለመንግስት፣ መንግስት ለህዝብ የሚታዘዙበት እንደማለት መሆኑን ጉጀራሻ አሰፋ አለማየሁ አብራርተዋል፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *