


የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን “የቡና ምርት ጥራት ለጋራ ብልጽግናችን” በሚል ቃል የንቅናቄ መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ አካሂዷል ፡፡
የቡናን ምርት በብዛት እና በጥራት በማምረት ሀገሪቱን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠብቅ ተገልጿል።
የንቅናቄው መድረክ ተሳታፊዎች በአርሶአደሩ ላይ የሚስተዋለውን የቡና ግብይት ስርዓትን ማዘመንና ህገ ወጥ የቡና ግብይትን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ።
በክልሉ የቡና ጥራትና ብራንድንግ፣ የቡና መረጃዎች ፣ የህገወጥ የቡና ግብይትእና የግብይት ስርዓቱ ላይ ተገቢው ትኩራት ሊደረግበት ይገባልም ብለዋል ተሳታፊዎቹ፡፡
የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኩጁአብ በቡና ዘርፍ አርሶ አደሩ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
በ2015 የበጀት ዓመት 64 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለመቅረብ ተቅዶ 42 ሺህ ቶን ቡና ማቅረብ የተቻለ ሲሆን አፈፃፀሙ ከዕቅድ አኳያ ዝቅተኛ መሆኑን አቶ በላይ አንስተዋል፡፡
ለዚህም ዝቅተኛ አፈፃፀም የምርት መጠን መቀነስ፣ የአለም አቀፍ የቡና ዋጋ መውረድ፣ የቡና ላኪ እና አቅራቢ በግብይት ወቅት አለመግባባት እና ህገወጥ የቡና ዝውውር መበራከት እንደሆነም የጠቆሙት አቶ በላይ በክልሉ ህገወጥ የቡና ዝውውር የሚገታበትን አሠራር በመዘርጋት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ ዮሐንስ መላኩ በበኩላቸው ክልሉ ሰፊ የመልልማትና ዉብ የተፈጥሮ ፀጋ የታደለ መሆኑን ጠቅሰዉ የቡና ሽፋንን 560 ሺህ 20 ሄክታር ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
የቅመማቅመም ምርት ሽፋንን ደግሞ ከ88 ሺህ 194 ሄክታር በላይ ማድረስ መቻሉን የገለፁት አቶ ዮሐንስ የሻይ ልማትን ወደ 2 ሺህ 276 ሄክታር ማድረስ መቻሉንም በንግግራቸዉ አንስተዋል።
ክልሉ በቡና፣ሻይና ቅመማቅመም ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገቱ ከክልሉም አልፎ ሀገርን መጥቀም በሚችል መልኩ ሰፊ ርብርብ እየተደረገበት ይገኛል ብለዋል አቶ ዮሐንስ።
መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለቡናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ሰፊ የንቅናቄ ስራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሻፊ ኡመር በቡና ምርት የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ቡናን በብዛትና በጥራት ማምረት እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የቡና ምርትና ጥራት ለማስጠበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከባለፈው አመት ጀምሮ ሰፊ የንቅናቄ ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ሻፊ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ በየደረጃው ያለው አመራር ለችግሩ መፍትሔ ሰጪ በመሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
