
የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ሁሉም ተማሪዎች በተማሩበት ሥርዓተ ትምህርት ይዘት እንደሚዘጋጅ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል፡፡
አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ ÷የ2017 ዓ.ም ተፈታኝ ተማሪዎች ከ9ኛ-10ኛ በነባሩ ሥርዓተ ትምህርት እንዲሁም ከ11ኛ – 12ኛ ደግሞ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተማሩ መሆናቸውን አንስቷል፡፡
ይሁን እንጂ በ2015 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ በናሙናነት በተመረጡ ት/ቤቶች የስርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ ላይ የተሳተፉ ት/ቤቶች ላይ የነበሩ ተማሪዎች 10ኛ ከፍልን በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት እንደተማሩ አመልክቷል፡፡
በአማራ ክልል በ2016 የትምህርት ዘመን መፈተን ሲገባቸው በጸጥታ ችግር ምክንያት ሳይፈተኑ የቀሩና የ11ኛ ክፍልን በነባሩ ሥርዓተ ትምህርት የተማሩ ት/ቤቶች ላይ የነበሩ ተማሪዎች በ2017 ዓ.ም የሚፈተኑ መኖራቸውንም ጠቅሷል፡፡
በመሆኑም የ2017 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከላይ የተገለጹትን ሶስቱንም ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንደሚዘጋጅ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ፈተናው ሁሉንም የዘመኑን ተፈታኝ ተማሪዎች በማከለ መንገድ ስታንዳርዱን፣ ደህንነቱንና ሚስጢራዊነቱን ጠብቆ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
ስለሆነም የፈተና ዝግጅቱ ከ9ኛ ከፍል ሙሉ በሙሉ ከነባሩ ሥርዓተ ትምህርት፣ ከ10ኛ ክፍል በነባሩና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ተመሳሳይ ይዘቶች፣ ከ11ኛ ከፍል በነባሩና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ተመሳሳይ ይዘቶች እና ከ12ኛ ከፍል ሙሉ በሙሉ ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት እንደሚዘጋጅ ተገልጿል፡፡
የኢኮኖሚክስ የትምህርት ዓይነት ግን በስርዓተ ትምህርቱ አዲስ የተጀመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በ12ኛ ክፍል ይዘት ላይ ብቻ ተመስርቶ እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል፡፡
ተማሪዎች ከ9ኛ -12ኛ ክፍል በየተማሩበት የሥርዓተ ትምህርት ይዘት ላይ በመመስረት ፈተናው እንደሚዘጋጅ አውቀው ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ አገልግሎቱ አሳስቧል፡፡
ሁሉም ተማሪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ወላጆች፣ መምህራንና መላው የትምህርት ማህበረሰብ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም ተጠይቋል ሲል ኤፍኤም ሲ ዘግቧል፡፡
