የምክር ቤት አባላት በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ዙሪያ የህዝብ መድረክ አካሄዱ

Spread the love

በካፋ ዞን፣የኦዲዮ ካካ ምርጫ ክልል የኢፈዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ተመራጮች በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ዙሪያ የህዝብ መድረክ በካካ ከተማ አካሂደዋል።

ከዚህ በፊት በህብረተሰቡ ሲነሳ የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት መንግሥት የልማት አቅሞችን በማቀናጀት እያደረገ ያለው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ያነሱት በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ክብርት ወ/ሮ ፋናዬ መለሰ ምላሽ ያላገኙ የህብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎችን ቀጣይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የአከባቢውን የኢኮኖሚ አቅም በመለየት በተቀናጀ መልኩ ወደ ልማት ማስገባት እንደሚገባ የጠቆሙት ክብርት ወ/ሮ ፋናዬ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ኑሮ ውድነት በመከላከል የቤተሰብ የገቢ አቅም በተገቢው ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አግልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሙስናና ብልሹ አሰራር በመውጣት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አግልግሎት በመስጠት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ክብርት የምክር ቤት አባሏ በዚህ ረገድ የሚስተዋሉና የህብረተሰብ የእሮሮ ምንጭ የኾኑ ጉዳዮች በመለየት በትኩረት መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ክብርት ወ/ሮ ፋናዬ አክለው በሁሉም መስክ ውጤታማነትን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተጨባጭ መፍታት እንደሚገባ ያነሱት ስሆን በምርጫ ክልሉ ህብረተሰብ ዘንድ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመንግሥት ቀርቦ ምላሽ እያገኘ መሆኑን አመላክተዋል።

የመሠረተ ልማት ተደራሽነች ችግር በወረዳው መኖሩን ያነሱት የመድረኩ ተሳታፊዎች መንግሥት የህብረተሰቡን የልማት አቅም በማቀናጀት የልማት ጥያቄዎችን መፍታት ይገባል ብለዋል።

መንግሥት በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት መኖሩን ያልሸሸጉት የመድረኩ ተሳታፊዎች ይሁን እንጅ የረዥም ጊዜ ጥያቄ የኾነው የካካ-ጭዳ መንገድ፣ የቦንጋ-ካካ መንገድ ጥገናና ደረጃ ማሻሻያ ፣ የድልድይ እና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት እንዲሁም በወረዳው ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አንስተዋል።

በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት መጠነ ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያነሱት የክልል ምክር ቤት አባል የተከበሩ ኢንጂነር በየነ በላቸው ህብረተሰቡ በልማትና መልካም አስተዳደር ግንባታ ስራዎች ዙሪያ ከመንግስት ጎን በመቆም እያሳየ ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ከዚህ በፊት በአከባቢው በስፋት ይነሱ የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት በተሰጠው ትኩረት አመርቂ ውጤት እየታየ መሆኑን ያመለከቱት የተከበሩ ኢንጅነር በየነ ምላሽ ያላገኙ የልማት ጥያቄዎችን በየደረጃው ባለው ምክር ቤት ለአስፈፃሚው በማቅረብ እንዲፈታ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላቶቹ በወረዳው እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እንዲሁም የካካ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የአግልግሎት አሰጣጥ ሂዴትን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

በመድረኩ የወረዳው ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገረመው ገብሬን ጨምሮ ሌሎች የወረዳው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *