
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ በመጠናቀቁ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን በቅርቡ እንደሚጀምር አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት አካታችና አሳታፊ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
በሦስት ዋና ዋና ምዕራፎች የተሳታፊዎች ልየታ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ በሂደቱ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር እና የሀገር ውስጥ እና ዓለም ዓቀፍ ተቋማትን በሂደቱ አጋር ሆነው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የተሳታፊ ልየታ ሥራ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የአጀንዳ ማሰብሳብ ሂደቱም በአብዛኛው ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በስኬት መጠናቀቁን አንስተዋል።
ሂደቱን ይበልጥ አካታች ለማድረግ ከሕዝባዊ መድረኮች በተጨማሪ በተለያዩ አማራጮች አጀንዳዎችን ሲሰበስብ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
ቃል-አቀባዩ አክለውም፤ ኮሚሽኑ በቀሪ ጊዜያት የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ባልተከናወነባቸው አካባቢዎች የማጠቃለል ሥራን እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ በመከናወኑ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደሚገባ አንስተው፤ ለዚህም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በዳያስፖራ ማህበረሰብ የአጀንዳ የማሰባሰብ ሥራን ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በፌፌራል ደረጃ ከሚገኙ ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚካሄድም አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በምክክሩ ሂደት እስካሁን የተሰባሰቡና በቀጣይ የሚሰባሰቡ አጀንዳዎችን የማደራጀትና የመቅረጽ ስራዎች እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩን የማካሄድ፣ ከምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን ማጠናቀር እና ተፈፃሚነታቸውን የመከታተል ስራዎች እንደሚተገበሩም ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ እስካሁን ባስመዘገባቸው ውጤቶች የሁሉም አካላት ተሣትፎ የላቀ እንደነበር በመጠቆም፣ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
