የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት የሚያስጠብቁ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው- ሚኒስቴሩ

Spread the love

የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን የሚያስጠበቁ አሰራሮች ትግበራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ተቋማት የጥራትና አሰራር አክሪዲቴሽን ስታንዳርድ ፍኖተ ካርታ በግብዓት ለማዳበርና ወደ ትግበራ ለማስገባት ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ እንደገለፁት የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በመለካት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት አስራሮች እየተዘረጉ ነው።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የጤና አገልግሎት የአክሪዲቴሽን ስታንዳርድ ፍኖተ ካርታ መሆኑን ጠቅሰው ይህም አዲሱን የጤና ፖሊስና ስትራቴጂ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።

ፍኖተ ካርታው የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የህክምና መርጃ መሳሪያዎች፣ የመድኃኒት አቅርቦት፤ የአሰራር ማዘመንና የህክምና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እውን ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አክለዋል።

በተጨማሪም በጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት ጥራት፤ የተቀናጀ የሀብት አጠቃቀም፣ የመድኃኒት ብክነትና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም እንደገለፁት በጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጥራት አስገዳጅ መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት የጥራት አገልግሎት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የህብረተሰቡን የጤና ፍላጎት ለማርካት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ጤና ስርዓት አስተማማኝና ተወዳዳሪ እንዲሆን መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የጤና ስርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አባስ ሀሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች የአክሪዲቴሽን ስታንዳርድ ፕሮግራም ትግበራ በተቋማቱ የሚሰጠው አገልግሎት ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሆስፒታሎች የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የአክሪዲቴሽን ስታንዳርድ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው ስታንዳርዱን ለመተግበር የአሰራርና የትግበራ ማኑዋል የማዘጋጀት ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የጥራት አክሪዲቴሽን ስታንዳርዱ ፍኖተ ካርታውና ማኑዋሉ የተዘጋጀው በጤና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ስታንዳርድ ኢንስቲትዩትና በኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት አማካኝነት መሆንም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *