በክልሉ በተለያዩ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ተገመገመ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በልማት አጋሮችና በሲቪክ ማህበራት የበጀት ድጋፍ የተከናወኑ ስራዎች የሀብት አመዳደብና ዝርዝር ተግባራት አፈጻጸም ራሱን አስችሎ በመገምገም ቀጣይ የጋራ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ በማስፈለጉ መድረኩ መፈጠሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸዋል።

በመሆኑም ፕሮጀክቶችን በየጊዜው በጋራ ማቀድና አፈጻጸሙን መገምገም የፍትሐዊነት ችግርን ለመፍታት ፣ ሀብቱ ለታለመለት ዓላማ ለማዋልና በአንዱ ያልተሸፈኑ አካባቢዎችን በሌላው በመሸፈን የማህበረሰቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

በፕሮጀክቶቹ አማካኝነት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ስራዎች መከናወኑንና ውጤቶች መመዝገቡን በማንሳት ከተለያዩ ምንጮች የሚመደቡ ሀብቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መስራትና ለዚሁም የአስተዳደር ስርዓቱ እያሻሻሉ መሄድ እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል ።

በየተቋማቱ የተመደበ ሀብት፣ የተሰማራው የሰው ኃይል፣ የታቀዱ ዕቅዶች ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ በውጤት መለካት ስለሚገባ በበቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ።

ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች የተቋማትን ግብ ላይ ያተኮሩ፣ ለዕቅድ አፈጻጸም ውጤት ላይ ድርሻቸውን የሚያበርክቱና በጊዜ የተገደቡ በመሆናቸው የሚሰሩ ስራዎችና መሠረተ ልማቶች ለማህበረሰቡ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ባለቤትነትን እያረጋገጡ መሄድ እንደሚገባ የገለጹት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸዉ ፕሮግራሞች በመንግስት ተቋማት በሚሰሩ ግቦችና ዕቅዶች ላይ ትኩረት በማድረግ ስለሚሠሩ በአግባቡ በማቀናጀት ውጤት ለማምጣት መስራት፣ የጋራ መድረኩን ቀጣይነትና የተሰሩ ተግባራትን በጠንካራ የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ስራ ማስደገፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል ።

በመድረኩ ላይ በግብርና፣በትምህርት እና በጤና ቢሮዎች በተለያዩ ፕሮጀክትና የፕሮግራሞች የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተመሣሣይ በሌሎች ተቋማት እንደሚቀጥል ከመድረኩ ተጠቁሟል ።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች፣ የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የፕሮግራምና ፕሮጀክቶች አስተባባሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *