







በክልሉ ፍትሃዊ የልማት ስርጭትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት በክልሉ ምዕራብ ኦሞ ዞን ቱም ከተማ የተገነባውን የንጹህ መጠጥ ውሃ መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው።
የክልሉ መንግሥት የህዝቡን መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ትኩረት አድርገው እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ ተመርቀው ለአግልግሎት የበቃው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህዝቡ የአከባቢው ሠላም በማስጠበቅ የመጡ ልማቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ዘላቂ አግልግሎት እንዲሰጥ፥ የውሃ አግልግሎት ማጠናከር የውሃ መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
የቱም ዉሃ ፕሮጀክቱ በአለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ መጋቢት 13 በሚከበረው የአለም የውሃ ቀን ተመርቀው ለአግልግት ክፍት መሆኑ ታሪካዊ እንደሚያደርገው የገለጹት የኢፌዴሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) የማጂ ቱም የውሃ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት አካላትን አመስግነዋል።
ክልሉ በከርሰ ምድርና በገፀ- ምድር የተፈጥሮ ዉሃ ሀብት የታደለ ቢሆንም የመንግስትን፣ የህዝብንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አቅም አቀናጅቶ ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ ሰፊ ክፍተት መኖሩን የገለጹት የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በዚህም ምክንያት የክልሉ ውሃ ሽፋን እጅግ አነስተኛ ሆኖ መቆየቱ አስታውሰዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ይህን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር የሚያስችል መጠነ ሰፊ ስራዎችን ሰርቶ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን የገለጹት ኃላፊው በዚህም ባለፉት 3 ኣመታት በክልሉ መንግስት 45 ፕሮጀክቶችን አጠንቀናል፤ በዞንና ወረዳ 108 አነስተኛ ፕሮጀክቶች፣ በመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች 112 አነስተኛ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በማህበረሰብ ተሳትፎ 5 ፕሮጀክቶች በጠቅላላ 270 ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ከ450ሺ ህዝብ በላይ የንጹህ መጠጥ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት የውለታ መጠናቸው 1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የኾኑ 26 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት መሆናቸውን የገለጹት ኢንጅነር በየነ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ወደ 150 ሺ የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍል የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በማድረግ ክልሉን የዉሃ ሽፋን በእጅጉ ከፍ የሚያደርግ ይሆናል ብሏል።
የቱም ከተማ መጠጥ ውሃ በክልላችን የዛሬ ሁለት ዓመት በየካቲት 21/ 2015 ዓ/ም በክልላችን ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የመሰረተ ድንጋይ በማኖርየግንባታ ስራው የተጀመረ ፕሮጀክት ነው፡፡
ግንባታው በዋናነት የ4 ምንጭ ግንባታና መልሶ ጥገና፣ 9.13 ኪሎ ሜትር ዋና የግፊት መስመር ዝርጋታ ስራ፣ 21.745 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ያለው የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ የከተማ ውስጥ ለውስጥ የውሃ ማሰራጫ መስመር ዝርጋታ፣ ሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ግንባታ (ባለ 200 ኪዩቢክ ሜትር እና ባለ 100 ኪዩቢክ ሜትር)፤ መቀነሻ ታንከር ግንባታ (ባለ 10 ኪዩቢክ ሜትር)፣ስድስት ቦኖዎች፣ የውሃ አገልግት ህንጻ ፣ የኬሚካል ህንጻ፣ የጥበቃ ቤት ግንባታ፣ እና አንድ ሞዴል የህዝብ መጸዳጃ ቤት ይገኙበታል፡፡
ፕሮጀክት በብዙ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር የተሳካ ፕሮጀክት ነው መሆኑ የገለጹት ኃላፊው የባለድርሻ አካላት ላደረጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግነው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የግንባታ ስራው የተጠናቀቀ ቢሆንም የወጪ መጋራት ድርሻ ከሚመለከታቸው አካላት ያልተሰበሰበ ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ኬኒ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የአከባቢውን የልማት ክፍተት ለመሸፈን የሰጠውን ትኩረት አድንቀው ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሻለ ጥራት ተገንብተው ለአግልግሎት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
የማጂ ቱም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በባስኬት ፈንድ ፕሮግራም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃ ልማት ፈንድ በኩል በተገኘ 55 ከመቶ ብድር እና 45 በመቶ በክልሉ መንግስት፤ ዞንና ከተማ አስተዳደር መሸፈኑም በመድረኩ ተገልጿል።
በዕድገቱ በዛብህ
