የበሽታ ቅኝትና አሰሳ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር የህብረተሰቡን ጤና መታደግ እንደሚገባ ተገለፀ

Spread the love

በካርተር ሴክተር በጀት የሚደገፉ የኦንኮ ሰርኪያሲስ፣ በዝሆኔና የጊኒ ዎርም መከታተልና ቁጥጥር የ5ዓመት ፕሮጀክት ዕቀድ ላይ ባለድርሻ አካላት መክረዋል ።

የኦንኮ ሰርኪያሲስ፣ በዝሆኔና የጊኒ ዎርም መከታተልና ቁጥጥር ስራዎች በክልሉ ባለፉት 5 ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን የቃኘ የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በፈረንጆቹ ከ2025_2029 ተግባራዊ በሚደረገው ዕቅድ ላይም ተሳታፊዎች ውይይት አድርገዋል።

ተሳታፊዎች በቀረቡት የመወያያ ሰነዶች በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ በሽታዎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰራው ስራ ሊመሰገን የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል ።

በቀጣይ 5 ዓታት ተግባራዊ የሚደረገው ይኸው ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአሰር ሂደት ወቅት ችግሮች እንዳይገጥሙ ከወዲሁ የህብረተሰቡን ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የግብዓት አቅርቦት ስራዎች ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል ።

በዘርፉም የሚስተዋለውን የመረጃ አያያዝና አላላክ መሠረታዊ ክፍተቶች ከወዲሁ በመለየት ሊቀረፉም እንደሚገባ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር ውጤታማ እንዲሆንም የድጋፍና ክትትል ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ የደቡብ ምዕራብ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ እሸቱ በሰጡት ማብራሪያ ውጤታማ ስራዎችን ከሚጠበቅብን ኃላፊነት አንጻር መፈጸም ይገባናል ብለዋል።

በቀጣይ 5 ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው ዕቅድ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች እንዳይከሰቱ ከወዲሁ ወረዳን መሠረት ያደረገ ዕቅድ ሊታቀድ ይገባልም ሲሉ አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል ።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመንግስታት ትብብር ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ዓለሙ ለፕሮጀክቱ ማሳኪያ የተፈቀደው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የክትትልና የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ተሳታፊ አካላት ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ መድረኩን ሲያጠቃልሉ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ፕሮጀክቶች ተግባራዊ የሚደረጉባቸው አካባቢዎች የህብረተሰቡን ጤና ለመታደግ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል ።

በካርተር ሴንተር ሊሰሩ በታቀዱ በኦንኮ ሰርኪያሲስ፣በጊኒ ዎርምና ዝሆኔ በሽታዎች ህብረተሰቡን ከእነዚህ በሽታዎች ለመታደግ ትክክለኛ እና ጥረቱን የጠበቀ መረጃ ማደራጀት በሁሉም መዋቅሮች ተጠናክሮ ሊደራጅ ይገባልም ብለዋል።

በካርተር ሴንተር ባለፉት 5 ዓመታት በተከናወኑ እና በቀጣይ 5 ዓመታት ተግባራዊ ሊደረጉ በተያዙ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ሲደረግ የነበረው የምክክር መድረክ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ተጠናቋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *