




ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አፋር ክልል በመገኘት የክልሉን የግብርና እና የኢንደስትሪ አቅሞች የሚያሳዩ ቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
ጉብኝታቸው ከስድስት ወራት በፊት ምርት የጀመረውንና 15 ቶን በሰዓት የሚያመርተውን የአዮዳይዝድ ጨው ማምረቻ ምልከታን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም በአፋር ክልል የተሳካ የበጋ ስንዴ ምርት እየተካሄደበት ያለውን ልማት ሥራ እና የአይሮላፍ መኖ ባንክ ልማት ማዕከልንም ጎብኝተዋል።
በክልሉ ስላለው የግብርና አቅም የነበረውን የተሳሳተ ምልከታ በማሸነፍ በመስኖ የለማ አስደናቂ የስንዴ ምርት ማግኘት ተችሏልም ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባውን እና ከማሳ ወደ ገበታ ሙሉ የምግብ ምርት ሰንሰለት የሚያጎላውን ዘመናዊ የዳቦ ፋብሪካም መርቀዋል።
ፋብሪካው በተገጠሙለት ዘመናዊ ማሽኖች በመጠቀም 420 ኩንታል ስንዴ በቀን መፍጨት የሚችል ሲሆን፤ 300 ሺህ ዳቦዎችንም በ24 ሰዓታት ማምረት እንደሚችል ተገልጿል።
