በጋምቤላ ክልል አኙዋ ዞን ጎግ ወረዳ የሚኖረው አቶ ኡጁሉ ኡሞድ የወዳደቁ ፕላስቲክ እቃዎችን እና ፌስታሎችን በመሰብሰብ የቤንዚን እና የናፍታ ነዳጅ ማምረት ችሏል።
የወዳደቁ ፕላስቲኮችን እና ፌስታሎችን ሲሰበስብ ሰዎች እንደ እብድ ይቆጥሩት እንደነበር የገለጸው አቶ ኡጁሉ፤ የወዳደቁ የፕላስቲክ እቃዎችና ፌስታሎችን በመሰብሰብ የቤንዚንና ናፍታ ነዳጅ በመስራት ውጤታማ መሆኑን ገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት የነዳጅ ምርቱ በጀነሬተር እና በሞተር ሳይክል ተሞክሮ ያለምንም እንከን ውጤታማ መሆኑን አቶ ኡጁሉ ተናግሯል።
በቀጣይ የጀመረውን ስራ በሰፊው ለመስራት ዕቅድ እንዳለው አቶ ኡጁሉ መግለፁን ከጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በጎግ ወረዳ ተገኝተው የአቶ ኡጁሉን የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ ያደረጉት በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሯች ባየክ፤ በጋምቤላ ክልል ለወጣቶች የስራ እድል የመፍጠርና ስራ ፈጣሪዎችን የማበረታታት ተግባራት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ለስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰናይ አኩዎር በበኩላቸው፤ ግለሰቡ እያከናወነ ያለው የፈጠራ ስራ ተጠናክሮ ቢቀጥል ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የግለሰቡ ስራ ጅምር ቢሆንም ሌሎች ወጣቶችን በስሩ በማሳተፍ ስራውን አስፋፍቶ እንዲሰራ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የአኙዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኡቶንግ ኡጁሉ የፈጠራ ስራው ተስፋ ሰጪ በመሆኑ የመስሪያና የማምረቻ ቦታ በመስጠት ስራውን አጠናክሮ እንዲሰራ ዞኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ኢቢሲ
