ተማሪዎች ስለ ግብር እና ታክስ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ በአሰባሰብ ሂደት የራሳቸዉን ሚና መወጣት ይገባቸዋል:-አቶ አልማዉ ዘዉዴ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የገቢዎች ቢሮ ከኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ክልላዊ የታክስና ጉምሩክ ክበብ ተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፥ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ በታኪስ አሰባሰብ ሂደት የራሳቸዉን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ ግብርና ታክስ በታማኝነት የመክፈል ባህል ማሳደግ እንደሚገባ ያስረዱት አቶ አልማው በትምህርት ቤት ደረጃ በታክስ ህግ ተገዥነት ላይ የሚደረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

ትምህርት ቤቶች ዜጎችን በቀለም እውቀትና በስነ-ምግባር ከማነጽ በተጓዳኝ በታክስና ግብር ላይ ከመሠረቱ በቂ እውቀት እንዲጨብጡ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ አልማው ተማሪዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ሁለንተናዊ እውቀትና ግንዛቤ በመጨበጥ እንዲሁም በትምህርታቸው ውጤታማ በመሆን ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና አከባቢያቸውን ለመለወጥ መትጋት እንደሚጠበቅባቸውም ጨምሮ ገልጸዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ

እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠዉ እና ዋናዉ የታክስ አይነት ቀጥታ ያልሆነ ታክስ ቢሆንም ህብረተሰባችን እና ግብር ከፋያችን ግንዛቤ እጥረት እንዲሁም ለታክስ ህጉ ተገዥ ያልሆኑ ጥቂት ግብር ከፋዮች በመኖራቸዉ ከዘርፉ ማግኘት ያለብንን ገቢ እያገኘን አለመሆኑን ጠቁመዋል።

“ከቀጥታ ያልሆነ ታክስ እንዲጨምር የአስተምሮ ስራችን ዋናዉ በመሆነ በተለያዩ አደረጃጀቶች ስልጠናዎች እና ምክክሮች እያደረግን እንገኛለን” ያሉት ኃላፊዋ በየትምህርት ቤቶች የተጀመረዉ የታክስ እና ጉምሩክ ክበብ ዋና አላማዉ መጪዉ ትዉልድ የታክስ እና ጉምሩክ አስተዳደር ምንነትን እና ህጎች ላይ መሰረታዊ እዉቀት እንዲኖራቸዉ በማድረግ ህጉወጥነትንና ኮንትሮባንድን የሚፀየፍ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ጠቁመዋል።

ተማሪዎች ወላጆቻቸዉን እና ማህበረሰቡን በማስተማር እና እራሳቸዉም ስሸምቱ እና አገልግሎትን ሲቀበሉ ደረሰኝ ጠይቀዉ በመገበያየት የገቢ ህግ እንዲከበር አምባሳደር በመሆን የድርሻቸዉን መወጣት ይገባልም ብለዋል ወ/ሮ ህይወት።

ዉድድሩም በሁሉም የክልሉ ት/ትቤቶች የተከናወነ እንደሆነና የዞን ማጠቃለያ የአሽናፊዎች አሽናፊ በዛሬ ዕለት የክልሉ አሸናፊ የሚሆኑት በክላስተር ከጅማ ዞን፣ ከጋምቤላ ክልል ጋር ተወዳድሮ 1ኛ የወጣ ተወዳዳሪ በሀገር አቀፍ የታክስ እና ጉምሩክጥያቅና መልስ ዉድድር ተሳታፊ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ስለ ግብርና ታክስ ተገዥነት በቂ እውቀት መያዝ እንደሚገባ የገለጹት በገቢዎች ሚኒስቴር የጅማ ቅርንጫፍ ምክትል ስራ-አስኪያጅ አቶ ነጋሳ አብዲሳ በዚህም መሠረት በትምህርት ተቋማት የተጀመረው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነም ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን የታክስና የግብር ህጎችን በተገቢው ለማስፈጸም የሁሉም ዜጋ ትብብር የሚሻ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ያስችል ዘንድ ግብርና ታክስ በአግባቡ መሰብሰብ የሚገባ እንደሆነም ተናግረዋል።

የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድሩ የእለቱ ተጋባዥ እንግዶች እና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *