
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በግብርናው ክፈለ-ኢኮኖሚ በርካታ ለዉጦች መመዝገባቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተደድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የሰባት ዓመታት የለውጥ ጉዞና የተገኙ ትሩፋቶችን በሚመለከት በጽ/ቤታቸው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግልጫ ሰጥተዋል።
መጋቢት 24/2010 ዓ/ም የለውጡ መንግሥት ወደ መንበረ ስልጣን ሲመጣ፥ ሀገሪቱ ዘርፈብዙ ችግሮች ውስጥ እንደነበረች ያወሱት አቶ ማስረሻ፣ ባለፉት ዓመታት ለውጡ እነኚህን ውስብስብ ችግሮች ለመሻገር ስልት ቀይሶ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ በመቻሉ ሁለንተናዊ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል።
“ከሰባት ዓመታት በፊት መጋቢት 24 የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበዓል ስመታቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው ያደረጉት ንግግር ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥና የዕድገት ጉዞ ፍኖተ ካርታ ሆኖ እያገለገለ ነው” ያሉት አቶ ማስረሻ ትውልዱ የተገኙ ድሎች ማስቀጠል እና ለአዳዲስ ድሎች መዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች አንዱ የግብርናው ክፈለ ኢኮኖሚ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ማስረሻ በዚህም በግብርናው ዘርፍ የተጣሉ አምስት አንኳር ሀገራዊ ትልሞችን ለማሳከት በክልሉ ዘርፍ ብዙ ተግባራት ተከናውነው በሂዴቱም አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ከፌዴራል በወረዱና በክልሉ መንግሥት ተግባራዊ የተደረጉ የተለያዩ ሀገራዊ ኢንሼቲቦች በተገቢው በማሳለጥ በምግብ ራስን የመቻልና የቤተሰብ ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ፤ በተለይ በክልሉ የስትራቴጂክ ኤክስፐርት ምርት የማሳደግ እንዲሁም የገቢ ተኪ ምርቶችን በስፋት በማምረት በዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማሳደግ መጀመሩን አስረድተዋል።
በዚህም፥ በዋና ዋና ሰብሎች ከክልሉ ምሥረታ በፊት ከነበረበት አነስተኛ የማሳ ሽፋንና አመታዊ የምርት መጠን አሁን ላይ 18.4 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ የተቻለ ሲሆን የሆልቲካልቸር አመታዊ ምርት መጠንም ከነበረበት 42.5 ሚሊዮን አሁን ላይ ወደ 52.3 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉን ተናግረዋል።
“የተገኘው ውጤት በየደረጃው ባሉት የዘርፉ ተዋናይ ብርቱ ጥረት እንዲሁም የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህል በማሳደግ፣የመስኖ መሠረተ ልማትና የውሃ አማራጭ ማስፋፋት በመቻሉ ነው” ያሉት አቶ ማስረሻ ይህም ተግባር በአጠቃላይ የግብርና ዘርፉ ግቡን ከማሳካት ረገድ ውጤታማ ነበረ ብሏል።
የክልሉን የልማት ፀጋዎች በውል በመለየት ወደ ሚጨበጥ ሀብት ለመቀየር በተሰጠው ልዩ ትኩረት በተላይ በቡናና ሻይ እንዲሁም የቅመማ ቅመም ምርቶችን የማሳ ሽፋን በማሳደግ ምርታማነትን መጨመር መቻሉን ተናግረዋል። በአመት ከ30 ሺ ቶን በላይ ለማዕከላዊ ገበያ ከማይቀርብበት ሁኔታ በመነሳት በአማካይ 54ሺህ ቶን ቡና ከክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ማስረሻ ይሁን እንጅ ይህ አሀዝ በአመት ከሚመረተው ምርት አንኳያ አነስተኛ በመሆኑ ዘርፉ ልዩ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ አልሸሸጉም።
በክልሉ ተኪ የግብርና ምርቶችን በስፋት በማምረት የአርሶአደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግና የሀገር ውስጥ የገበያ ፋላጎት ለማሟላት በተሰጠው ትኩረት በሩዝ፣ስንዴ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ምርት አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ያስረዱት አቶ ማስረሻ ክልሉ በምግብ ራስን በመቻል ከተረጂነት ለመላቀቅ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብሏል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ከክልሉ ምሥረታ ወዲህ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው አንድ ቢሊዮን ገደማ ችግኞች በክልሉ መተከላቸውን የገለጹት አቶ ማስረሻ የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት ከምግብ ዋስትና ጋር ቀጥተኛ ግኑኝነት ያላቸው በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በቀጣይ ጊዜያትም የክልሉ ግብርና ከማምረት ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነት በቤተሰብ ደረጃ የማረጋገጥ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስረዱት ኃላፊው በዘርፉም የክልሉን አርሶናአርብቶ አደር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት የማረጋገጥ ተግባር ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
