
የመጋቢታዊያን የለውጥ ትሩፋቶችን አስመልከቶ የክልሉ የውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በዉሃ፣በመስኖና በማዕድን ዘርፍ የተመዘገቡ ድሎችን የዕይታ ለውጥ እና ሽግግርን ጭምር ያመጡ መሆናቸዉን ገልጸዋል ።
ኢንጂነር በየነ በመግለጫቸው ከለውጡ በፊት ዘርፉ እንደሀገር ብዙ ትኩረት ያልተሰጠበት መሆኑን በማስታወስ አሁን ዕምርታዊ ለውጥ መምጣቱን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተሰጠው ትኩረት በርካታ የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም ወደ ማጠናቀቅ የተመጣበት መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ሌላው የውሀ ፖለቲካ ጉዳይ የባህር በር ሲሆን ከለውጡ በፊት ጥያቄ ማንሳት የማይቻል፣ እንደወንጀል የሚቆጠር ጉዳይ ሆኖ ተዳፍኖ የቆየውን የለውጡ መንግስት በሰጠው ትኩረት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ/አጀንዳ ሆኖ መቅረብና በዲፕሎማሲው ዘርፍ የለውጡ መንግስት ባስመዘገው ዕምርታ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት መቻሉን ጨምረው ተናግረዋል ።
መጋቢት 24 ሀገራችን ከበርካታ ፈተና እና የቁልቁለት ጉዞ ላይ በነበረችበት ወቅት የሚያሻገር የብልጽግና ሀሳብ የፈለቀበት ቀን በመሆኑ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያውያን በተለይም ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ልዩ ቀን መሆኑ ገልጸዋል።
ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ ያለውን አቅሞችን በመለየት ኃይልን በማሰባሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተሰራው መጠነ ሰፊ ስራ የክልሉ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ሽፋን ከ3 ዓመት በፊት ከነበረበት 32.7% አሁን ወደ 43.7% በማድረስ ከ450 ሺህ በላይ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል ።
በተጨማሪም ከ26 በላይ የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች በክልሉ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
በመስኖ ዘርፍ ክልሉ ብዙም ልምድ ያልነበረዉ ነገር ግን መሠረታዊ የዕሳቤና ዕይታ ሽግግር እንዲመጣ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ በለውጡ መንግስት በተሰራው ስራ የእይታ ለውጥ የተደረገበትና የበጋ ስንዴ ልማት ለመስኖ ልማት ዘርፍ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል ።
ከዚህም በመነሳት በክልሉ ውስጥ የመንግስት፣ የህብረተሰብና የልማት አጋሮችን ቅንጅት ግንባታው ከዚህ በፊት ተገንብቶ የቆሙትን ወደ ስራ በማስገባትና 15 መለስተኛ የመስኖ አውታሮችን በመገንባት 3627 ሄ/ር ማልማት ወደሚችልበት ደረጃ ክልሉ መድረሱን እንዲሁም ከ11 በላይ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸዉን የቢሮ ኃላፊው አንስተዋል ።
አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በዘላቂነት ለማላቀቅ በሰፊው እንዲያለሙ ለማስቻል ትላልቅ የመስኖ አውታሮችን በማጥናት ከ15 ሺህ 700 ሄ/ር በላይ ለማልማት የሚያስችል የሻርማ መስኖ ጥናት ተጠናቅቆ ለፌደራል መንግስት መቅረቡን አንስተዋል።
በግንባታ ሂደት ላይ ያሉት ፕሮጀክቶችንና በጥናት ላይ ያሉትን ወደ ስራ በማስገባት የክልሉን ተጠቃሚነት ከ3627ሄ/ር ወደ 40 ሺህ ሄ/ር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል ።
ከለወጡ መንግስት በፊት የሀገራችን ፖሊሲው ግብርና መር ከመሆኑ የተነሳ የማዕድኑ ዘርፍ የተረሳና የሀብትና የብልጽግና ምንጭ ተደርጎ የማይታወቅ መሆኑን በማስታወስ ከለውጥ ወዲህ በተሰጠው ትኩረት አመርቂ ውጤት ከተመዘገበበት የመጋቢት 24 ፍሬዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል ።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዚህ ምቹ የሆነ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመነደፉ በእሳቤ ደረጃ ለውጥ መምጣቱን ጨምረው አንስተዋል።
ክልሉ እንደ ወርቅ፣ ብረታብረት ፣ የድንጋይ ከሰልና የመሳሰሉት ማዕድናት ክምችት በሰፊው የሚገኝበት ቢሆንም ካለው ፀጋ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን የገለጹት ኃላፊዉ አሁን ላይ ለዉጥ እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
ወርቅን ከባህላዊ የአመራረት ዘዴ ወደ ዘመናዊ ለማሻገር በተደረገው ጥረት አምራቾች ዘመናዊ የማጠቢያ ማሽን እንዲጠቀሙና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉ ባለሀብቶችን በዘርፉ ለማሳተፍ ብሎም በዘርፉ የሚታየውን ህገወጥነትን ለመከላከል በተደረገው ጥረት የዛሬ 3 ዓመት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው በየዓመቱ ይገባ ከነበረዉ 60ኪ.ግ ከነበረበት ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት ብቻ ወደ 105 ኪ.ግ በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የድንጋይ ከሰል ማዕድን በሰፊው የሚገኝ ክልል በመሆኑ ዕምቅ አቅሙን በመገንዘብ የፌደራል መንግስት በሰጠው ትኩረት የሀገሪቱን 25 በመቶ ፍላጎት መሸፈን የሚያስችልና በሰዓት 150 ቶን ማጠብና ማበልፀግ የሚችል ፋብሪካ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አስተዳደር ተገንብቶ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በዘርፉ በተፈጠረው መነቃቃት 460 ሺህ ቶን የድንጋይ ከሰል ወደ ፋብሪካ በመላኩ ሀገሪቱ ለሲሚንቶ ምርት ግብዓትነት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ሀገር የሚያመጣውን ወጭ ማትረፍ መቻሉ እንዲሁም በማዕድኑ ዘርፍ ከ15 ሺህ በላይ የስራ ዕድል መፈጠሩ ለዘርፉ የተሰጠ ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ መሆኑን ኢንጂነር በየነ ገልጸዋል ።
በለውጡ መንግስት በተሰጠው ትኩረት፣ በተደረገው ሁሉ አቀፍ ርብርብና ቅንጅት የተመዘገቡ ድሎችንና የዕይታ ለውጥ እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም ለቀጣይ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት በመስራት ክልሉንም ሆነ ሀገርን ከዘርፉ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል ።
በጌታሁን ግርማ
