




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ በልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ስትራቴጅዎችና ፖሊሲዎች ፤በገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን እና ዲጂታላይዜሽን ላይ ለካፋ ዞን የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ተግባራዊ በማድረግ የገጠርና ከተማ ዕድገት ማመጣጠን እንደሚገባ የገለጹት የቢሮው ኃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ ስልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች የመንግሥት ዓላማና ተልዕኮ ለመፈጸም ግንዛቤ የሚያሳድግ እንደሆነ ተናግረዋል።
የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን አርሶአደሮች በሚያመርቱት ምርት ላይ ዕሴት በመጨመር የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግዛው በዚህም በገጠር የብድርና የማሽን አቅርቦት ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የካፋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው መንግስት በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሰራ መሆነ ተናግረዋል።
በካፋ ዞን 6 ወረዳዎች የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ኢንሼቲቭ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት አቶ ተፈሪ ግብርና ውጤቶችን ከኢንዱስትሪ ጋር በማጣጣም የአርሶአደሮች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከስልጠናው በቂ ዕውቀት በመውሰድ በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን ፈጥኖ ማረም እንደሚገባ ያሳሰቡት የቢሮ ምክትል ኃላፊና የኢኖቬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስፋው የመንግሥት አግልግሎት በአይሲቲና በኢኖቬሽን በማስደገፍ ማቀላጠፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአግልግሎት አሰጣጥን በዘላቂነት ለማሻሻልና ቀልጣፋ ለማድረግ የአይሲቲ እውቀትና ክህሎት ማሳደግ ይገባል ያሉት አቶ ምትኩ በዚህም በኮደርስ ስልጠና ለክልሉ የተሰጠውን ኮታ በተገቢው በመጠቀም መሰልጠን ይገባል ብለዋል።
የቢሮ ምክትል ኃላፊና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ከርቅነሽ ሻንቆ በበኩላቸው፥ በገጠር ኢንዱስትሪን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩ በማድረግ እንደሀገር በዘርፉ የተቀመጠውን ተልዕኮ ማሳካት እንደሚገባ የገለጹት ወ/ሮ ብርቄ የአከባቢውን የኢንዱስትሪ ፀጋዎች መለየትና ወደ ተጨባጭ ሃብት የመቀየር ተግባር መጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል።
በስልጠና መድረኩ ላይ የካፋ ዞን እና የተመረጡ የስድስት ወረዳዎች የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
