የክልሉን ህዝብ ባህል፣ወግና የአኗኗር ዘዴን ታሳቢ ያደረገ የቤተሰብ ህግ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቆመ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፍትህ ቢሮ ከዩኒሴፍ በኘሮግራም ጋር በመተባበር የክልሉን የቤተሰብ ህግ ማውጣት አስፈላጊነት ፣ ከሴቶች እና ህጻናት መብት ከማስከበር እና ከሚደርስባቸው ጥቃት ከመከላከል አኳያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በሚዛን አማን እየተካሄደ ይገኛል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፣ቤተሰብ የሁሉም ህብረተሰብ መሠረት በመሆኑ በህገመንግስቱ በተሰጠው መብት መሠረት በህግ ጥበቃ እንዲደረግለት የቤተሰብ ህግ ማውጣት እና ለተግባራዊነቱም በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።

እስከአሁን በነባሩ ክልል የወጣው የቤተሰብ ህግ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አውስተው የክልሉን ህዝብ ባህል ፣ወግና የአኗኗር ዘዴን ታሳቢ ያደረገ ህግ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በክልሉ የቤተሰብ ህግ ለማርቀቅ ሀገር በቀል ዕውቀቶች እና እሳቤዎችን በማካተት በትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የቤተሰብ ህግ ማውጣት አስፈላጊነት፣ከሴቶች እና ህጻናት መብት ከማስከበር እና ከሚደርስባቸው ጥቃት ከመከላከል አኳያ የመነሻ ጽሁፍ በቢሮው የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዳይሬክተሬት ዳይሬክተርና የዩኒሴፍ ፎካል የሆኑት በአቶ ይንገስ ታደለ እየቀረበ ያለ ሲሆን በቀረበው ሰነድ ላይም ውይይት ይደረጋል።

በምክክር መድረኩ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት፣ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ፣ከርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት፣ከክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ፣ከስነምግባር እና ፀረሙስና ቢሮ ፣እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *