



የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተገልጿል
የሁሉቱ ተቋማት ሀላፊዎችና የማኔጅመንት አባላት በጋራ መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ውይይት አድርገዋል።
የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለረዥም አመታት በሚዲያው ዘርፍ የህብረተሰቡን የመረጃ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ግንባር ቀደም በመሆን እያገለገለ የሚገኝ የሚዲያ ተቋም እንደሆነ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም ገነሞ አስረድተዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚ የተቋሙን የረዥም ጊዜ ልምድና አደረጃጀትን መነሻ በማድረግ አዲስ በመደራጀት ላይ የሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ጠንካራ የሚዲያ ተቋም እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና በትብብር እንደሚሰራም ገልፀዋል።
የሚዲያ ተቋሙን በቴክኖሎጂ፣ በስልጠና፣ በማማከርና በሌሎች ጉዳዮች ለማብቃት ያላቸውን ፍቃደኝነትም አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
የይዘት ጥራትና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ብቃትና ፍጥነት ለሚዲያ ተቋም ጥንካሬ ወሳኝ ስለሆነ ዘርፉን በልዩ ትኩረት መምራት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ መኩሪያ በበኩላቸው ተቋሙ በክልሉ በመረጃ የበለፀገና በልማት ስራዎች የነቃ ተሳታፊ የሚሆን ማህበረሰብን ለመፍጠር በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ተግባር እየገባ ያለ የሚዲያ ተቋም መሆኑን አስረድተዋል።
ተቋሙን ወደ ስራ ለማስገባት በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የገለፁ አቶ መንግስት ከደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር በቅንጅት መስራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያስችላል ብለዋል።
ሚዲያ ኔትወርኩ እያከናወነ ያለው ትግባር የሚበረታታ እንደሆነ ተጠቁሟል።
ለተቋሙ ስኬታማ አደረጃጀት የሚያስችሉ ስራዎችን ደረጃ በደረጃ ማደራጀትና በቂ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ጠንካራ የሚዲያ ተቋም ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ ልሰራ እንደሚገባም ከስምምነት ተደርሷል።
በመጨረሻም የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስኪያጅ የሚዲያ ኔትወርኩን የእስከአሁኑ የስራ እንቅስቃሴ አስጎበኝተዋል።
