
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጤና ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል ፡-
የክልሉ ጤና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጤና ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የማህበረሰቡን ጤና ለማስጠበቅ በተሰራው ሥራ ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የወባ ወረርሽኝ መከላከል እና መቆጣጠር፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆነ በሽታ፣ኤችአይቪ ኤድስ፣የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት፣ የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት እንዲሁም የጤና አገልግሎት ዲጅታላይዝ ማድሰግ እና መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ሥራዎች መሰራታቸው ተመላክቷል።
በሽታን በመከላከልና አክሞ በማዳን ሂደት ብሎም በአገልግሎት አሰጣጥ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ረገድም ሥራዎች ተሰርቷል።
የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እንዳስታወቁት፤ ባለፉት ወራት የጤና ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል።
በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ረገድም የወባ ህመም ኖሯቸው ምርመራ የተደረገላቸው 1 ሚሊዮን 483 ሺህ 319 ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 922,253 ሰዎች የወባ ተዋሲያን በደማቸው ተገኝቷል።
የወባ ማግኘት ምጣኔው 62 በመቶ ሲሆን ወባ የተገኘባቸው ሰዎችም አስፈላጊው ህክምና ማግኘታቸውን የጠቆሙት አቶ ኢብራሂም በክልሉ ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው 42 ወረዳዎች ቤት ለቤት 1 ሚሊዮን 144 ሺህ 762 የአልጋ አጎበር ስርጭት ተደርጓል ብለዋል።
ወቅታዊ የወባ ሁኔታን በተመለከተ በክልላችን በሁሉም ዞኖች ባሉት በአብዘኛው ወረዳዎች ዋና የጤና ችግር ወባ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው በተደረገው መጠነ ሰፊ ርብርብ የወባ በሽታ ጫና የቀነሰ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ወቅት ከዝናብና ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ሊያገረሽ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን በተገቢው በመለየት የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራ በሁሉም የክልላችን አከባቢዎች በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ኢብራሂም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም ሳይቋረት በትኩረት መሠራት እንደሚገባው በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡
የቲቢና የኦንኮሰርኪሲስ በሽታዎችን የመከላከል እና መቆጣጠር ሥራ መሥራቱን የገለፁት ኃላፊው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልን በተመለከት 383,122 የደም ግፊት በሽተኞች ልየታ የተደረገ መሆኑን ጠቅሶ ከእነዚህም ውስጥ 11,751 (3%) ሰዎች ከፍተኛ የደም ግፊት ተጠቂ በመሆናቸው አስፈላጊዉ የህክምና ክትትል እንዲያገኙም ተደርጓል ብለዋል ።
የኤች አይቭ ኤድስን በሚመለከት 134,969 ሰዎች የኤች አይቪ ምርመራ ከተደረገላቸው ውስጥ 766 (0.57%) ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘ ሲሆን እነዚህም 279 ወንዶችና 487 ሴቶች ናቸዉ ያሉት አቶ ኢብራሂም በዘጠኝ ወራት 67,869 የነፍሰጡር እናቶች የኤችአይቪ ኤድስ ምክርና የምርመራ አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቁመው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው 72 እናቶች የጸረ ኤች አይቪ ኤድስ መድኃኒት እየወሰዱ ይገኛሉ።
የስኳር ህሙማን ልየታ በተመለከተ 73,846 ሰዎች ላይ ልየታ መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው ከእነዚህም መካከል ከእነዚህምዉስጥ 1,822(2.4%) ሰዎች የስኳር ታማሚ መሆናቸዉ ታዉቆ አስፈላጊው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አስረድተዋል።
የማህጸን በር ካንሰር ልየታና ህክምና አንጻር በዘጠኝ ወራቱ ከ30-40 ዓመት የሆኑ ሴቶች ላይ በንቅናቄና በመደበኛ ሥራ 4,443 ሴቶችን በመለየት ከዚህም ውስጥ 275 ሴቶች የቅድመ ካንሰር ምልክት የታየባቸው ሲሆኑ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛልም ብለዋል።
በእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት 351,874 የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን 84,491 እናቶች የቅድመ ወሊድ አገልግሎት አግኝተዋል ያሉት ኃላፊው 46,916 እናቶች በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የእናቶች ወሊድ አገልግሎት ያገኙ ሲሆን 62,620 እናቶችና ጨቅላ ህጻናቶች አገልግሎት መስጠት ተችሏል።
በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች ዕድሜያቸው ከ1ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የክትባት አገልግሎት መስጠት የተቻለ ሲሆን በዚሁ መሠረትም ለ76,850 ህጻናት ፔንታ 3 እና ለ73,398 የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን ያብራሩት ኃላፊው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ሥርዓተ ምግብ ልየታ ከማድረግ አኳያ 253, 338 ሆጻናት የስርዓተ ምግብ ደረጃ የመለየት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚሁም ልየታ ከተደረገላቸው ህጻናት መካከል 27,074 የመካከለኛ የምግብ እጥረት እና 8,389 ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያለባቸው በመሆናቸው የህክምና ክትትልና የሙያ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ያሉት አቶ ኢብራሂም በክልሉ በ7 ወረዳዎች የተመጣጠነ ምግብ ማድረስ መቻሉንም የጠቆሙት ኃላፊው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3704 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።
የእናቶችና የህጻናት ጤና እንዲሁም ድንገተኛ የጤና አገልግሎት በሁሉም ክልሉ አከባቢዎች ማሻሻል ይረዳ ዘንድ ዘጠኝ አምቡላንስ እና 30 ሞተር ሣይክል ለሁሉም ዞኖች ድጋፍ መደረጉንም ጨምረው ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ክልላዊ ማዐጤመ ማቀጣጠያ ንቅናቄ ከክልል እስከ ወረዳ ደረጃ በመካሄድ ወደ ሥራ መገባቱን የተናገሩት አቶ ኢብራሂም እስካሁን 162,765 አዳድስ አባላት ማፍራት መቻሉን ጠቁመው 258,776 (89.3%) ነባር አባላት እድሳት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህም አጠቃላይ አባላት ምጣኔ 75.62% መድረሱን የተናገሩት አቶ ኢብራሂም 433 ሚሊዮን 665 ሺህ 541 ብር ለመሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የመድሃኒት እና የህክምና መሳሪያ አቅርቦትን በተመለከተም ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒት፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በክልል ደረጃ ለጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ እና ህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል።
በክልሉ የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት በከተሞች ለማስፋፋት ሲሰራ መቆየቱን የጠቀሱት ኃላፊው በዚህም አራት ማህበረሰብ መድኃኒት ቤትና አምስት የቀይ መስቀል ፋርማሲዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸውም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪም በስድስት ከተሞች ማለትም ሚዛን አማን፣ኦዳ፣ዋቻ፣ ባቹማ፣ ማጂ ቱም እና ጀሙ ከተሞች የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
በማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዘጠኝ ወራት ማጅራት ግትር፣እከክ በሽታ እና በሌሎች መሠል በሽታዎች በደረሰው ርፖርት መሠረት ናሙና በመውሰድና በሽታ የተገኘባቸው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙም ተደርጓል።
ህገወጥ የመድኃኒት ዝውውር፣ኮንትሮባንድ እና ተራድኦ እና ምንጫቸው ያልታወቁ መድሃኒቶች በክልሉ ባሉት የመድኃኒት ቤትና የጤና ተቋማቶች ላይ በተደረገው ቁጥጥርና ክትትል 41 ሚሊየን 127 ሺህ 722 ብር የሚያወጣ መድኃኒት በመያዝ የአስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደበትም ገልጸዋል።
የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ድጂታላይዝድ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን በመጠቆም በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የጤና ተቋም መሠረተ ልማቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቁ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት አቶ ኢብራሂም ተማም።
በዚህም በኮንታ ዞን የደልባ ገነት የ2ኛው ትውልድ የጤና ኬላ ግንባታ መጠናቀቁን እና ግንባታው የቆመው የቤንች ሸኮ ዞን የአዲስዓለም 2ኛው ትውልድ ጤና ኬላ ወደ ሥራ መግባቱንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
በካፋ ዞን ቆንዳ እና በዳውሮ ዞን የዋካ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ 93 በመቶ የደረሱ ሲሆኑ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቁ ይሆናል።
በማከልም ሌሎች በበጀት እጥረት፣የግንባታ እቃ መናርና የተቋራጮች አቅም ውስንነት አቅም ማነስ ምክንያት ለረጅም የቆሙ 11 ግንባታዎች ውል በማቋረጥ ከክልሉ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር ውል በመግባት 4 ግንባታዎች ሥራ በመጀመር ግንባታቸው እየተፋጠነ ይገኛልም ብለዋል ኃላፊው ።
በፍቅር ከበደ
