ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያሳልጥ፣ጊዜ ቆጣቢና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል:-ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር)

Spread the love

ክልላዊ የፋይዳ ብሔራዊ ድጂታል መታወቂያ ይፋዊ ማስጀመሪያ ስነስርዓት በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል ።‎

በክልሉ እስከ በጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ከ150 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ኢኒሼቲቩን በይፋ ባስጀመሩበት ዕለት ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያሳልጥ፣ጊዜ ቆጣቢና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል።

የፋይዳ ብሔራዊ ድጅታል መታወቂያ ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሁሉም ዜጎች ያለማመንታት መታወቂያውን ማውጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ ።

የፋይዳ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ በሀገራችን የድጅታል ኢኮኖሚ ልማትን ለማፋጠን ከወሰደችሁ አንኳር ተግባራት ውስጥ አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀሙ በምናከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ፣ምርትና ምርታማነትን ለማሳለጥ የሚያግዝ በመሆኑ ይበልጥ ማላቅና ማስቀጠል ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

ፋይዳ ብሔራዊ ድጅታል መታወቂያ ከፓስፖርት በተለየ መንገድ ሰፋ ያሉ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚቻልበት እንደሆነም አብራርተዋል ።

በክልሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቅርቡ በክልሉ ይጀመራልም ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ባስተላለፉት መልዕክት ሀገር በቀል ሪፎርም ከተደረጉት ተግባራቶች አንዱ የሆነው ፋይዳ ብሔራዊ ድጂታል መታወቂያ ዘር፣ቀለም፣ብሔርና ሐይማኖት ሳይለይ ወጥ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል ።

‎የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከሚያግዙ ኢኒሼቲቦች ‎የፋይዳ ብሄራዊ ዲጅታል መታወቂያ ድርሻው የላቀ ነው ብለዋል።

በይፋዊ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፣የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣የየዞን አመራሮች እና የመንግስት ሰራተኞች ተገኝተዋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *