



የኢትዮጵያን የብልጽግና ሕልሞች ለማሳካት ኹሉም በላቀ ደረጃ የድርሻዉን መወጣት እንዳለበት የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር) አሳሰቡ። የአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞች “የመሐል ዘመን” በሚል ርእስ በተዘጋጀዉ ሀገራዊ ሰነድ ላይ በተወያዩበት ወቅት ክቡር ሚኒስትሩ እንዳመላከቱት ተቋማት እና ግለሰቦች የተጣለባቸዉን ኃላፊነት በብቃት፣ በጥራትና ወቅቱ በሚጠይቀው አግባብ መወጣት ከቻሉ የኢትዮጵያ የብልጽግና ሕልሞች የሚሳኩ ለመኾናቸው ያለፉት ዓመታት ስኬቶች ምስክሮች ናቸው።
የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የተሰጠዉ ኃላፊነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ማስገንዘብ፣ የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ መነሣሣቶች፣ ዕቅዶች፣ አፈጻጸሞች እና ውጤቶች ማሳወቅ መኾኑን ያመላከቱት ዶ.ር ለገሠ ዘርፉን በአጀንዳ መምራት እና በኢትዮጵያና ብሔራዊ ጥቅሞቿ ላይ የሚመዘዙ አጀንዳዎችን በብቃት መመከት ትኩረት ሊሰጠዉ እንደሚገባም አስገንዘብበዋል።
የመሐል ዘመን በሚል ርእስ የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ደግሞ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ከነበረችበት ሁኔታ መሰረታዊ በሆነ መልኩ እድገት ያስመዘገበች መሆኑን በመጥቀስ ይህንን ለውጥ ወደፊት ለማስቀጠልና ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ በውስጥና በውጭ ያሉ ክፍተቶችንና ተጋላጭነቶችን ነቅሶ በማውጣት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። “ሃገራችን በለውጥ ሂደት ያለፈችው የለውጡን ቀልባሽ ኃይሎች በመርታት ብቻ አይደለም፤ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን ጭምር በመሻገር እንጅ። ድርቅ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽ፣ የእርስ በርስ ግጭትና መፈናቀል ለውጡን የፈተኑ ጉዳዮች ነበሩ” ብለዋል። የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት እና የለውጡ አመራር ቁርጠኝነት እና ብስለት የተሞላበት አመራር ለውጡን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገራቸውንም አቶ ተስፋሁን አብራርተዋል።
የሕዝብን ጥያቄዎች በመመለስ፣ አካታች የፖለቲካ ሥርዐት በመዘርጋት፣ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማድረግና ዕድገቱን በማስቀጠል፣ የትርክት ለውጥ በማድረግና ፈተናዎችን በመቋቋም በርካታ ስኬቶች በየዘርፉ መመዝገባቸውን አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ እነዚህ ስኬቶች የፈጠሩት መለስተኛ እርካታ ወደማይቀለበሰው የብልጽግና መዳረሻ የሚደረገዉን ጉዞ እንዳያሰናክሉ በብስለት ማለፍ እንደሚገባ ተመላክቷል። ለዚህም በስኬቶች ሊደበቁ የሚችሉ ውስጣዊ ክፍተቶችን ያለማቅማማት መፍታት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በውይይቱ የተሳፉት የአገልግሎቱ አመራር እና ባለሙያዎች ሰነዱ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰና ተጨባጭ ኹኔታዉን ያገናዘበ መኾኑን ገልጸዋል። ሀገራዊ የለውጥ ጉዞዉ ያለበትን ደረጃና ቀጣይ የሚጠይቀውን ጥረት በእጅጉ እንደተረዱበት ተናግረዋል።
