




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ትስስር አሰራር ላይ ያተኮረ ስልጠና ለዞን አመራርና ለባለሙያዎች እንዲሁም ለአልሚ ባለሀብቶች በቦንጋ ከተማ ሰጥቷል።
በመድረኩ የውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ክልሉ በተፈጥሮ ጸጋ የተቸረዉ እንደመሆኑ መጠን ይህንን መልካም ስነ ምህዳር እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ምርትና ምርታማነት በመጨመር የኢኮኖሚ አቅምን ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል።
የመድረኩ አስፈላጊነት በዋናነት በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮ ች ላይ ማለትም በቡና፣ ሻይ ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ትስስር ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን የገለፁት አቶ አስራት ገልጸዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላትና አልሚ ባለሃብቶች ምርቱን ትስስር በመፍጠር ከአካባቢዉ ካለዉ አርሶ አደር ጋር የምርት ግብይት እድል በመፍጠር የገበያ ዕድል ለማመቻቸት ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
አቶ አስራት አክለውም እንደ ሀገር የተቀመጠዉን አቅጣጫ በመከተል እንደ ክልላችን መዉሰድ ያለብንን ድርሻ ወስደን በልዩ ትኩረት እስከ ታችኛዉ መዋቅር ድረስ በመዉረድ ምርቶቻችን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን አቅም ለማጎልበት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ትልቅ ሚና አለዉ ብለዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጆአብ በበኩላቸዉ ከክልል እስከ ዞን እና ወረዳ ባለዉ መዋቅር ያለዉ አርሶ አደር፣ ባለሀብት የኮንትራት እርሻ ዉል በመግባት ምርቱን ማሳደግ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር በማዘመን ምርቶቻችንን በጥራት እንደተጠበቀ የገቢያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነዉ ብለዋል።
በስልጠናዉ የካፋ ዞን ግብርና፣ ደንና አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባ መጫ በበኩላቸው ክልላችን ብሎም ዞናችን በግብርናዉ ዘርፍ ከሚታወቅበት አንዱ ዋነኛዉ የሆነዉ የቡና ፣ ሻይ ቅመማ ቅመም ምርት መሆኑን አዉስተዉ ምርቱን ለማሳደግ እንደ ሀገር በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሠረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ስልጠናዉ በየጊዜዉ መሰጠቱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዉ ሁሉም ሰልጣኝ ወደ ተግባር የመግባቱ ሁኔታ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለው የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ አርሶ አደሩም ሆነ ባለሀብቱ የየራሱን ድርሻ ወስዶ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በፀሐይ በላቸው
