





በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ሲካሄድ የቆየውና ሊጠናቀቅ አንድ ቀን የቀረው ክልል አቀፍ የወንዶች እግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድር አስተባባሪ አካላትና ወጣቶች የውድድር ሂደት በሚመለከት አስተያየት ተሰጥተዋል ።
ስፖርት ጤንነትን ከመጠበቅም በላይ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና አንድነት እንዲሁም ለቱሪዝም ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳለ የገለጹት የክልሉ ባህል ቱርዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አህመድን አወል ናቸው።
በመሆኑም በዓመት አንድ ጊዜ ውድድሩን ከመጠበቅ ባሻገር በየአካባቢው ከታች ጀምሮ በመስራት ታዳጊ ስፖርተኞችን በማፍራት የክልሉ ስፖርት ዕድገት ላይ አሻራ ማሳረፍ ይገባል ብለዋል።
አክለውም የዘንድሮ ውድድር በስፖርተኞችም ሆነ በደጋፊዎች ዘንድ የተሻለ የስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት መሆኑን በመግለጽ ጤናማና ሠላማዊ የሆነ ውድድር በማካሄድ በስፖርታዊ ዲስፕሊን ለማጠናቀቅ እንዳገዘ ተናግረዋል።
የክልሉ የእግር ኳስ የፌደሬሽኑ ም/ፕሬዝዳንትና የውድድሩ ስነስርዓት ኮሚቴ ስብሳቢ የሆኑት አቶ አበበ አስፋው ውድድሩ በቀጣይ ዓመት ለሚመሠረተው የክልሉ ሊግ መሠረት የሚጥል እንደሆነ አንስተዋል ።
ስፖርት ብዙ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን በማሳደግ ስፖርትን ህዝባዊ መሠረት ማስያዝ እንደሚሻ ተናግረዋል ።
ውድድሩ በሀገር ደረጃ ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችና ቡድኖችን ከመለየትም በላይ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠሪያ መሆኑን የገለጹት በክልሉ ባህል ቱርዝምና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ዳይረክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ በየነ ቴቃ ናቸው።
ስፖርትን ህዝባዊ መሠረት በማስያዝ ጠንካራና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚሻ በማንሳት በዘርፉ የተፈጠረው መነቃቃት እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በሁሉም አካባቢ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል ።
ኮሚሽነር ጌታሁን ጅረታ የእስካሁኑ ውድድር ሂደቱ ጤናማ፣ ልምድ የተወሰደበት እና ጠንካራ ውድድር መንፈስ የታየበት እንዲሁም የተለያዩ አካባቢን የወከሉ ስፖርተኞችን ያገናኘ መድረክ በመሆኑ ዘርፌ ብዙ ጠቀመታ መኖሩንም ገልጸዋል ።
የከተማው ህዝብ የእንግዳ ተቀባይነትና ደጋፊዎች የራሱን ክለብ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የተጫወተውን በሚዛናዊነት ሲደግፉ የታየበት እንደሆነም አክለዋል ።
ውድድሩ ለአካባቢ ወጣት በእግር ኳስ ስፖርት ዘርፍ መነሳሳት የፈጠረና አንዱ ከሌላው የልምድ ልውውጥ ያደረገበት እንዲሁም ለህዝቦች ባህልና ዕሴት ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን የተናገሩት ወጣት አብዮት መንገሻ እና ወጣት ምስጋናው ወጋ ናቸው
በመሆኑም ወጣቱ ትውል ራሱን ከአልባሌ ቦታ በመቆጠብ ዘላቂነት ያለው ልምምድ በማድረግ ለክልሉ የእግር ኳስ ዕድገትም ሆነ በሀገር ደረጃ ክልሉን በመወከል አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል ።
በመጨረሻም አስተያየት ሰጪዎቹ ስፖርታዊ ጨዋነት አስተሳሰብን መገንባት ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ከማጎልበትም በላይ ለስፖርቱ ውድድር ሂዴትም ሆነ በአጠቃላይ ለክልላዊ ስፖርት ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በጌታሁን ግርማ
