











ባለፈው ሳምንት በዚህ አምድ አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ የሚያሳይ ፅሁፍ ማጋራታችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከክልላችን ዞኖች አንዱ የሆነውን የምዕራብ ኦሞ ዞንን እንቃኛለን፡፡ መልካም ንባብ!
የምዕራብ ኦሞ ዞንየደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ከመሠረቱት ስድስት ዞኖች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ዞኑ በሰሜን በኩል በቤንች ሸኮ ዞንና እና በካፋ ዞን፤ በደቡብ በኩል በደቡብ ሱዳን ሀገር፤ በምስራቅ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እና በምዕራብ በኩል በጋምቤላ ክልል ይዋሰናል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ከ14ሺህ 584 ስኩዋር ኪሎሜትር በላይ የቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን ይህም ከክልሉ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው ዞን ያደርገዋል፡፡ የዞኑን የአየር ንብረት በተመለከት 57.4% ቆላ፣ 34% ወይና ደጋ፣ 8.6% ደጋ ሆኖ የሙቀት መጠኑም ዝቅተኛ 15.1 ዲግሪ ሴሊሽየስ ሲሆን ከፍተኛ ደግሞ 27.5 ዲግሪ ሴሊሽየስ ነዉ። ዓመታዊ የዝናብ መጠኑም ከ400 ሚሊሜትር እስከ 2000 ሚሊሜትር የሚደርስ ነው፡፡
የምዕራብ ኦሞ ዞን በሰባት ወረዳዎች፣ በሶስት የከተማ አስተዳደሮች፣ በ18 የከተማ ቀበሌዎች እና በ96የገጠር ቀበሌዎች (በድምሩ በ114) ቀበሌዎች የተዋቀረ ነዉ፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ጀሙ ሲሆን ከአዲስ አበባ 662 ኪሎሜትር እንዲሁም ከክልሉ የአስተዳደርና የፖለቲካ መቀመጫ ከሆነው ቦንጋ ከተማ በ186 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የ1999 ዓ.ም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትን መሠረት በማድረግ በተደረገው ትንቢያ በ2016 የበጀት ዓመት የዞኑ ህዝብ ብዛት 328,019 (162,063 ወንድ እና 165,956 ሴት) እንደሆነ የሚገመት ሲሆን ይህ በሰፈራ መልክ የመጡት እንዲሁም በበሮ በረሃማ አካባቢ ያሉት አልተካተቱም፡፡
የምዕራብ ኦሞ ዞን ሰፊ የቆዳ ስፋትና የተለያየ የአየር ንብረት ያለዉ በመሆኑ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አከባቢ ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያለበት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ወርቅ፣ የኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ የድንጋይ ከሰል፣ የኮንስትራክሽን ማዕድናትና የጨው አፈር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡በተጨማሪም ዞኑ በበርካታ የእርሻ ምርቶች የሚታወቅ ሲሆን በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሩዝ፣ ሰልጥ እና ሌሎች የአገዳ ሰብሎች በዞኑ በስፋት ይመረቱበታል፡፡ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ እዉቅና ያገኘዉ የጎሪ ጌሻ ቡና የሚገኝበት ሲሆን በቅመማቅመም ምርቱም በኮሮረማ ይታወቃል፡፡
ከቱርዝም አኳያም የኦሞ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ከ71 በላይ ለቱሪስት መሲህብ የሚሆኑ እንደ ፏፏቴ፣ የፍል ውሃ፣ አኮቦና ኦሞ ፤ኪሉ ፤ዳል፤ ኦልሙ ፤ሾሩም እና ኪብሽ ወንዞች ያሉ ስፍራዎች እንዲሁም የሱሪ ብሄረሰብ የዶንጋ ጨዋታ ይገኙበታል፡፡
ከጤናና ትምህርት ተቋማት ተደራሽነት አኳያ በዞኑ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣ 16 ጤና ጣቢያዎች እና 96 ጤና ኬላዎች የሚገኙ ሲሆን 191 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 14 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲሁም እንዲሁም ሁለት የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ይገኝበታል፡፡
በመቀጠልም የጨዉ አፈር በመኤኒት ሻሻ ወረዳ ዉስጥ የሚገኝ ሲሆን በዞኑ ከተማ በ60 ኪ/ሜ ርቀት ዉስጥ ይገኛል የቀርካሃ የተፈጥሮ ደን በመኤኒት ሻሻ ወረዳ ዉስጥ የሚገኝ ሲሆን በዞኑ ከተማ በ52 ኪሎ ሜትር ርቀት ዉስጥ ትገኛለች ፡፡
አኩ ፏፏቴ በማጅ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ከዞኑ ከተማ በ106 ኪ/ሜ ርቀት ዉስጥ የሚገኝ እንድሁም የእግዜር ድልድይ በተመሳሳይ በማጅ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ከዞኑ ከተማ በ97 ኪ/ሜ ርቀት ዉስጥ ትገኛለች ቀጥሎም፤ በተመሳሳይ የጣሊያን ጡብ ቤቶች በማጂ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ከጀሙ ከተማ በ109 ኪሎ ሜትር ዉስጥ ይገኛል፤ባድል ዋሻና ፏፏቴ በመኤኒት ጎልድያ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን በዞኑ ከተማ በ68 ኪሎ ሜትር ዉስጥ ትገኛለች፤ ፃና ፏፏቴ በቤሮ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ከዞኑ ከተማ በ276 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ፤በተዋሊ ትክል ድንጋይ በጎሪ ጌሻ ወረዳ ዉስጥ የሚገኝ ሲሆን ቦታዉ ከጀሙ ከተማ በ84 ኪሎ ሜትር ውስጥ ትገኛለች፤ ምዕራብ ኦሞ በበርካታ የተፈጥሮ ደን የሚገኙበት ዞን ለምሳሌ ከብዙ በጥቅቱ የጎር የተፈጥሮ ደን እና የያርጣ የተፈጥሮ ደን ይጠቀሳሉ።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ከ71 በላይ የቱሪስት መስህቦች የሚገኝበት እና ከእነዚህ ዉስጥ 1 ብቻ በመልማት ላይ ያለ ማለትም ኦሞ ብሄራዊ ፓርክ ብቻ እየለማ እንደሚገኝ ተመላክቷል ፡፡
በፓርኩ ልዩ ልዩ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ይገኝበታል፡፡ በብሄራዊ ፓርኩ ከ75 በላይ አጥቢ እንስሳትን ፤ ከ325 በላይ የአዕዋፍ ዓይነቶችን እንደያዘ የሚነገረዉ ኦሞ ብሄራዊ ፓርክ ዉድንቢዎችን ፣ የመጋላ ቆርኪ መንጋ ፣ ሳላዎች ፣ የሜዳ ፍየሎች እና ሌሎች አጥቢ እንስሳቶችም ይገኛሉ፡፡
ዉድንቢ ደግሞ በኢትዮጵያ በኦሞ ብሄራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ የዱር እንስሳት ነዉ ፡፡ ፓርኩ ደግሞ ከምዕራብ ኦሞ ዞን በ184 ኪ/ሜ ርቀት ዉስጥ ይገኛል፡፡
ዞኑ ከፍተኛ የሆነ የዉኃ ሽፋን ያለበት ቢሆንም ግን የመጠጥ ዉኃ ሽፋኑ 31.05% ብቻ ነዉ።
ምዕራብ ኦሞ ዞን 4ት ነባር ብሄረሰቦች ያሉት ሲሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመምጣት ተቀላቅለዉ የሚኖሩ ህዝቦች ጭምር ይገኛሉ ፡፡
4ቱ ነባር ብሄረሰቦች መኤኒት ፣ዲዚ ፣ሱሪ እና ዝልማሞ ናቸዉ እነዚህ ብሄረሰቦች የራሳቸውን የሆነ ባህል፤ ታርክ ፤ቅርስ ፤ቋንቋ እሴቶች አሉዋቸው።
እነዚህ ብሄረሰቦች የራሳቸውን ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያስተዋውቅበት የራሳቸውን የሆነ አለባበስ አመጋገብ እንዲሁም የባህላዊ ዳኝነት እና የለቅሶ ሥራዓታቸዉ አሉዋቸው።
በዚህም የመኤን ብሄረሰቦች በ4 ወረዳዎችና በ2 ከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ሲሆን ዲዚ በሁለት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ተዋቅሮ ይገኛል ፡፡
ቀጥሎም የሱሪና የዝልማሞ ብሄረሰቦች በአንድ ወረዳ እየተዳደሩ የሚገኙ ሲሆን ዞኑ በያዛቸዉ 7 ወረዳዎች እና 3 ከተማ አስተዳደሮች ማለትም በ 10 መዋቅሮች ዉስጥ 4 ነባር ብሄረሰቦች እና የተለያዩ ብሄረሰቦች በፍቅር እየኖሩ ይገኛሉ፡፡
ከመሰረተ ልማት አንጻር ዞኑ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም የመሰረተ ልማት ችግሮች ግን በስፋት ይታይበታል በዚህ መሰረት ከመንገድ ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንገድ ከባቹማ ከተማ እስከ ማጂ ወረዳ ያለው 124 ኪሎ ሜትር ስሆን ከዚህ ዉስጥ 16 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ 108 ኪሎ ሜትር በጠጠር የተላበሰ መንገድ ነዉ መንገዱም በERRA ነው የተሰራው።
ቀጥሎ በመገንባት ላይ ያለው ከማጂ እስከ ሳይ 33 ኪሎ ሜትር አስፓልት ለብሶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በምዕራብ ኦሞ ዞን በአጠቃላይ የመንገድ ተደራሽነት በፌዴራል በክልሉ እና በአርብቶ አደር ቢሮ በኩል 49 ኪሎ ሜትር አስፓልት እና 556 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድ ያላት ዞን ነው።
በተፈጥሮ የበለጸገች ምዕራብ ኦሞ ለመኖር ሚቹ ለኢንቨስትመንት ሚቹ እና በማር ፤በወርቅ እንዲሁም በተፈጥሮ ለልማት ሚቹ የሆነ ዞን ነው።
በዚህም 74 የአልሚ ኢንቨስተሮች ሲኖሩ 68 በግብርና 6 በእንዱስትሪ ተሰማርተዉ በሥራ ላይ ናቸዉ።
አካባቢዉም አርብቶ እና ከፊል አርሶ አደር ማህበረሰብ የሚገኝበት ዞን ነው የ ምዕራብ ኦሞ ዞን፡፡
