








የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮች የ2017 ዓ/ም ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ የበልግ ወቅት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ማስጀመሪያ ጎን ለጎን በቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ ከእርሻ ቦታ ባህርዛፍን በማንሳት በፍራፍሬና ሰብል የተሸፈነውን ማሳ የመስክ ምልከታ ተደርጓል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በእርሻ ቦታ ላይ ያለውን ባህርዛፍ በማንሳት በፍራፍሬና በሰብል በመተካት የአርሶ አደሩን ገቢ ምንጭ ከማሳደግም በላይ በክልሉ ተረጂነትን ለማስወገድና የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ እንደሆ አንስተዋል ።
በወረዳው ባሉት ቀበሌዎች እየተሰሩ ያሉ ባህርዛፍን በፍራፍሬ የመተካት ስራ ለክልሉ አካባቢዎች ምርጥ ተሞክሮ ከመሆንም ባሻገር በበጋ ወቅት የተሰራውን ስነ አካላዊ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራን በስነ ህይወታዊ ከማስደገፍ አንጻር ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።
የሰሜን ቤንች ወረዳ በባህር ዛፍ የተሸፈነ የእርሻ መሬትን በበቆሎ ፣በሙዝ ፣ በአቡካዶ እና በቡና በመቀየር እያሳየ ያለው ሥራ ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።
በክልሉ የመሬት መጠቀሚያ ግብር አዋጅ ላይ ባህርዛፍ በእርሻ መሬት መትከል ለየት ያለ የመሬት መጠቀሚያ ግብር እንዲከፈል ሲደረግ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥም በላይ በእርሻ መሬት ላይ በስፋት የሚካሄደውን የባህር ዛፍ ተከላን ለመግታትም የሚሰራውን ስራን ውጤታማ ለማድረግ እንደሆነ አንስተዋል።
የተሰሩ ስራዎችን ቀጣይነት ባለው መንገድ መደገፍ፣ ማበረታታት እና ከገበያ ጋር ማስተሳሰር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚፈለግ ተግባር እንደሆነ ተጠቁመዋል ።
የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉበላ በበኩላቸው ከአርሶ አደሩ ጋር በመግባባት በወረዳው በ21 ቀበሌዎች ከ3000ሄ/ር
በላይ መሬት ባህርዛፍን በማስነሳት በሙዝና በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን ገልጸው የሰሪቲ ቀበሌ 1000ሄ/ር ማሳ ለዚሁ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በወረዳው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም(FSRP) ፕሮግራም የተገነባው የቢር የፍራፍሬ አትክልት የግብይት ማዕከልን ፣የቦሰቃ የችግኝ ጣቢያ ጉብኝት በማድረግ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል ።
በጌታሁን ግርማ
